ረቡዕ ነሐሴ 29 ቀን 2016 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሳያውቅ የኤርፖርት ግንባታ እንዳያካሂድ መመሪያ እንደተሰጠው አስታውቋል።
የኤርፖርቶችን ተደራሽነት ፍትሐዊ ለማድረግ እንዲቻል፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሳያውቀው ኤርፖርት እንዳይገነባ መመሪያ እንደተሰጣቸው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ማስጀመርያ መርሐ ግብሩን ነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲያካሂድ በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገልጸዋል።
አየር መንገዱ ብሔራዊ የኤርፖርቶች የልማት ፕላን እያዘጋጀ መሆኑን የገለጹት አቶ መስፍን፣ ይህንንም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እየተከታተለው መሆኑን አስታውቀዋል፤ ‹‹ከእያንዳንዱ ክልል ኤርፖርት ሥሩልን የሚል ብዙ ጥያቄ ይቀርብልናል›› ያሉት ዋና ሥራ አሥፈጻሚው፣ እየተዘጋጀ ያለው ፕላንም ይህን ጫና የሚቀንስ ይሆናል ብለዋል።
አዲስ አበባን ጨምሮ 23 ኤርፖርቶች መኖራቸውንና በአሁኑ ወቅትም ተጨማሪ የአምስት ኤርፖርቶች ግንባታ እየተካሄደ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ አቅራቢያ ስድስተኛ ኤርፖርት ለመገንባት ኮንትራክተር ተመርጦ የመሬት እርክክብ ብቻ እንደሚቀር አብራርተዋል።



