ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሊቀመንበር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) የሕወሓት እና ኤርትራ መሪዎች ይፋዊ ያልሆነ ዉይይት አካሂደዉ እንደነበር ገለጹ።
ደብረፂዮን (ዶ/ር) በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የኤርትራ ባለሥልጣናት እና ህወሓት የመጀመርያ ዉይይት የተካሄደዉ በተባበሩት አረብ ኤሜሪትስ ዱባይ ላይ ከስድስት ወር በፊት ነበር ብለዋል።
በዉይይቱ ላይ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸዉ ረዳ ህወሓትን ወክለዉ በዱባይ በተካሔዱ ዉይይቶች ላይ ተካፍለዉ እንደነበር ተናግረዋል።
የህወሓት ሊቀመንበሩ በዱባይ ከመጀመርያው ስብሰባ በኋላ ከኤርትራ መሪዎች ጋር ቀጣይ ስብሰባዎች መደረጉንም አመልክተዋል።
ይሁን እንጂ የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን(ዶ/ር) ስብሰባው የት እና መቼ ተደረገ የሚለውን ከመግለፅ ተቆጥበዋል።
የህወሓት ዓላማ ሰላም ለመፍጠር “የፋኖ ኃይሎችንና የኤርትራን መንግሥት ጨምሮ ከጎረቤቶቻችን ሁሉ ጋር ሰላም መፍጠር” ነዉ ሲሉ መናገራቸዉም ተሰምቷል።
ዶክተር ደብረፅዮን አክለውም ይህ ከኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት ጋር የተካሄደው ውይይት በህወሓት ሥራ አስፈጻሚና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዕውቅና መካሄዱን ገልጸዋል።



