ረቡዕ መስከረም 01 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) በዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ የሚመራው ኦሎምፒክ ኮሚቴ በ11 ባንኮች ያለውን ሂሳብ እንዳያንቀሳቅስ በፍርድ ቤት ታግዷል።
የኦሎምፒክ ተሳታፊ ብሄራዊ ፌዴሬሽኖችና በታዋቂ ግለሠቦች የተወከሉ ህጋዊ ጠበቆች ሐሙስ በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣በዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ እና በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ሥ/አ ቦርድ አባላት ላይ ክስ መስርተዋል።
በተጠቀሱት አካላት ላይ የቀረበውን የክስ አቤቱታ የተመለከተው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ላይ የዕግድ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ፍርድ ቤቱ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ገንዘብ ያንቀሳቅስባቸዋል ተብለው የተለዩ በሀገሪቱ የሚገኙ 11 ባንኮች ላይ ያለውን ገንዘብ ከትላንት ጳጉሜ 5/ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሌላ ውሳኔ እስኪተላለፍ ድረስ እንዳያንቀሳቅስ የዕግድ ትዕዛዝ ተላልፎበታል።



