ቅዳሜ መስከረም 18 ቀን 2017(አዲስ ማለዳ) ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የተራዘመ የብድር አቅርቦትን በተመለከተ የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል፡፡
አይኤምኤፍ ባወጣው መግለጫ ድርጅቱ በአራት ዓመታት የሚያቀርበው የ3.4 ቢሊዮን ዶላር የተራዘመ የብድር አቅርቦትን በተመለከተ የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተደርሷል ብሏል።
ስምምነቱ በይፋ በዓለም አቀፉ ገንዘብ ተቋም ዋና የአመራር ቦርድ ከታየ በኋላ ኢትዮጵያ ወደ 345 ሚሊዮን ዶላር ገደማ እንደምታገኝ ተገልጿል።
“በገበያ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመንን ጨምሮ ኢትዮጵያ አገር በቀል የምጣኔ ሃብት ፖሊሲ ማሻሻያ ማድረጓ በጥሩ ሁኔታ ውጤት እያሳየ ነው” ተብሏል።
በገበያ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን መተግበሩ በትይዩና በይፋዊ ገበያ መካከል ያለውን ልዩነት በስፋት እያጠበበ እንደሆነም ተጠቁሟል።
መንግሥት ያለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ በገበያ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመንን ለመተግበር ውሳኔ አሳልፎ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩ ይታወሳል።
ከዚህ ቀደም ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የብድር ስምምነት ላይ ሳይደርስ በኢትዮጵያ ለሳምንታት የዘለቀውን ቆይታውን ማጠናቀቁ ይታወሳል።
የድርጅቱ ተወካዮች አዲስ አበባ ሄደው በብድር ጉዳይ ውይይት ሲያደርጉ የቆዩት ኢትዮጵያ አገር በቀል የምጣኔ ሃብት ዕቅዷን ለመተግበር የሚያስችላትን የገንዘብ ድጋፍ ከተቋሙ መጠየቋን ተከትሎ መሆኑ ተመላክቷል።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ “ስኬታማ ለውጦችን ማድረጓ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን የሚፈጥር የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትን አስተማማኝ የሚያረግና ለዘለቄታዊ የምጣኔ ሃብት እድገት የሚረዳ ነው” ብሏል።
ያለፈው ዓመት ሐምሌ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የብድር ስምምነት ሊያጸድቅ መሆኑ መዘገቡ ይታወሳል።



