ቅዳሜ መስከረም 18 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሰላምና መረጋጋት በተገናኘ የሚቀርቡባትን ክሶችና ወቀሳዎች በፍጹም አትቀበልም ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ አስታወቁ፤ ሽብርተኝነትን ከመዋጋት የሚያግዳት ምንም ነገር እንደሌለም ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ይህን የገለጹት በኒውዮርክ እየተካሄደ በሚገኘው 79ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሽብርተኛነትን በመዋጋት ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥ እየሰራች እንደምትገኝ የገለጹት አምባሳደር ታየ #በሶማሊያ የሽብርተኛ ቡድን የሆነውን አልሻባብን አቅም በከፍተኛ ሁኔታ በማዳከም ረገድ ከሌሎች አገራት ሰላም አስከባሪ ሃይሎች ጋር ውጤታማ ተግባር ማከናወኗን አመልክተዋል።
ዓለም አቀፋ ማህበረሰብ በሶማሊያ የተገኙ ድሎችን ወደ ኋላ በመመለስ የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት ስጋት ላይ የሚጥሉ ድርጊቶችን ሊያስቆም እንደሚገባ አሳስበዋል።
አምባሳደር ታዬ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም የከፈለችውን መስዋዕትነትና ዋጋ እውቅና ልትሰጥና ልታከብር እንደሚገባም ገልጸዋል።



