ሰኞ መስከረም 20 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) ታጣቂ ሃይሎች በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ያሉ ትምህርት ቤቶችን እንደካምፕ እና የጦር መሳሪያ ማከማቻነት ሲጠቀሙባቸው ስለነበር ባለፉት አመታት በክልሉ የመማር ማስተማር ሒደቱ መስተጓጎሉን የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ረዳይ ገ/ እግዚአብሄር ተናግረዋል፡፡
አሁንም ድረስ 552 ትምህርት ቤቶቸ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መሆናቸውን የገለጹት አቶ ረዳኢ፤ መደበኛ የመማር ማስተማር ተግባሩን እያከናወኑ ያሉ ትምህርት ቤቶችም ስራቸውን በአግባቡ እየተወጡት እንዳልሆነ ነው የገለጹት፡፡
አሁን ላይ በክልሉ አጠቃላይ 2ሺ 492 ትምህርት ቤቶች እንዳሉ የገለጹት ኃላፊው፤ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተፈጸመ በኋላ የመማር ማስተማር አገልግሎት የሚሰጡ ትምህርት ቤቶች 1ሺህ 835 ብቻ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ በተያዘው የትምህርት ዘመን የጸጥታ ችግር ባለባቸው የአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ምዝገባ ያልተከናወነባቸው ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡


