በእነ ቀሲስ በላይ መኮንን መዝገብ ላይ ለ4ኛ ጊዜ ቀጠሮ ተሰጠ

0
295

ማክሰኞ መስከረም 28 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በእነ ቀሲስ በላይ መኮንን መዝገብ ላይ የምስክሮችን ቃል መርምሮ ብይን ለመስጠት ለአራተኛ ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በተከሳሾች ቄስ በላይ መኮንን፣ እያሱ እንዳለ ወ/መስቀል፣ በረከት ሙላቱ ጃፋር እና አለምገና ሳሙኤል ዲንሳ እና የኒሞና ንግድ ስራ ኃላ/የተ/የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ አበራ መርጋ ተስፋዬ በተባሉት ላይ ከባድ ማታለል ሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።

በዚህም ተከሳሾቹ ከአፍሪካ ህብረት ምንም አይነት የክፍያ ትእዛዝ ባልተሰጠበት ሁኔታ ላይ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር ለተከሰሱ ተከሳሾች በተለያዩ የዶላር መጠን ክፍያ ይፈጸምላቸው የሚል አጠቃላይ የ 6 ሚሊየን 50 ሺህ ዶላር ሀሰተኛ የክፍያ ሰነድ በአንደኛ ተከሳሽ መቅረቡ ተጠቅሶ በሁሉም ተከሳሾች ላይ ከባድ ማታለል ሙስና ወንጀል ክስ ተመስርቷል።

በቀረበው ክስ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ብቻ ችሎት የቀረቡና የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን÷ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች በአድራሻቸው ባለመገኘታቸውና በተደጋጋሚ ቀጠሮ ባለመቅረባቸው ለጊዜው ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል።

ከ1ኛ እስከ 3ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ክሱ እንዲሻሻልላቸው ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ነጥቦችን ፍርድ ቤቱ መርምሮ ወደፊት በማስረጃ እንደሚጣራ ገልጾ መቃወሚያቸውን አልተቀበለውም።

ከዚህም በኋላ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው ተከሳሾቹ የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ህግ የአፍሪካ ህብረት ቅርጫፍ የባንክ ባለሙያዎችን አጠቃላይ ሶስት ምስክሮችን አቅርቦ ምስክርነታቸውን አሰምቶ ነበር፡፡

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ህግ ምስክር ቃል መርምሮ ብይን ለመስጠት ከሐምሌ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሶስት ጊዜ ቀጥሮ ነበር፤ ይሁንና ዛሬም በነበረ ቀጠሮ በተለያዩ ስራዎችና ምክንያት መዝገቡ ተመርምሮ ተሰርቶ አለመጠናቀቁ መዝገቡን በሚመለከቱት ዳኛ በኩል ተገልጾ በድጋሚ ለ4ኛ ጊዜ ለጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም ተቀጥሯል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here