ሰኞ ጥቅምት 04 ቀን 2016(አዲስ ማለዳ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን ዛሬ ማለዳ የሶስት አርሶ አደሮች ህይወት ማለፉን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
አርሶ አደሩ በሰላም ወጥቶ መግባት አልቻለም ችግሩን ማስቆም የሚችል አካል እስካሁን አልተገኘም ሲሉ ነው ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት፡፡
“ለበርካታ አመታት ዝርፊያና ግድያው ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ተሻግረው በገቡ ታጣቂዎች ሲፈጸምባቸው እንደቆየ” እና እስካሁን ዘላቂ መፍትሄ እንዳልተሰጣቸው የገለጹት ነዋሪዎች በኮሬ ዞን 2ኛ ዙር የእርሻ ወቅት የሚባለው ከሐምሌ እስከ ጥቅምት ወር ሲሆን በዚህ ወቅት በእርሻ ማረስ፣ ከብት ጥበቃና እና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ በነበሩት ዜጎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት 11 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 4 ሰዎች የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸውም አመላክተዋል።
በአሁኑ ሰዓት ሁሉም አርሶአደሮች በእርሻ ማረም ላይ በመሆናቸው ጥቃቱ መበራከቱን እና በርካታ ንብረቶች መዘረፋቸውን አስታውቀዋል፡፡ አዲስ ማለዳ የአካባቢውን ባለስልጣናት በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ያደረገችው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም፡፡



