👉 ችግሩ ሙሉ በሙሉ ተፈቷል ለማለት አንደፍርም- የለሚ ኩራ ክ/ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ
ሐሙስ ጥቅምት 14 ቀን 2017(አዲስ ማለዳ)የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአራዳ ክፍለ ከተማ በፒያሳ እና አራት ኪሎ አካባቢዎች ይኖሩ የነበሩ ነዋሪዎች በኮሊደር ልማቱ ምክንያት ከቀድሞ የመኖሪያ መንደራቸው መነሳታቸው ይታወቃል፡፡
በመሆኑም ተለዋጭ ቤቶች እና ቦታዎችን በእጣ በማቅረብ በወጣላቸው እጣ መሰረት በለሚ ኩራ ክ/ከተማ ለልማት ተነሽዎቹ መኖሪያ ቦታን አስረክቧል፡፡
ነገር ግን እነዚህ የልማት ተነሺዎች አስቀድም ሲኖሩበት ከነበረው ሁኔታ የከፋ ችግር ገጥሞናል ያሉ ሲሆን ከነበሩበት አራት ኪሎ ተነስተው ለሚኩራ ክ/ከተማ ሳይት3 ጃርሶ አካባቢ በጋራ መኖሪያቤት ቦታ እንደተሰጣቸው የገለጹ ቅሬታ አቅራቢቆች መሰረተ ልማት ያልተሟላበት ለመኖር ከባድ የሆነ አካባቢ ላይ እንድንሰፍር ሆነናል ማለታቸውን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል፡፡
ይህ ዘገባ ከወጣ ወራትን ያስቆጠረ በመሆኑ አዲስ ማለዳ ምን አይነት መሻሻል እና የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ተከናውነዋል ስትል ዳግም ተመልክታለች፡፡
በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡት የለሚ ኩራ ክ/ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወንድማገኝ ታደሰ “ሙሉ ለሙሉ በቂ ነው የሚያስብል ባይሆንም አስቀድሞ ከነበረበት የተሻለ የግንባታ ለውጥ አለ” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በግንባታ ሂደት ላይ እንደሆነ ገልጸው የነበረ ቢሆንም አሁንም አለመጠናቀቁን እና በሂደት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ስራ አስፈጻሚው ይህንን ቢሉም ነዋሪዎች አሁንም የመሰረተ-ልማት ጉዳይ በአሳሳቢነቱ ስለመቀጠሉ ያነሳሉ አክለውም አሁንም የነበርንበትን ቦታ እንድንናፍቅ ሆነናል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢ ነዋሪዎቹ ይህ ነው የሚባል ለውጥ እንዳልመጣ ገልጸዋል
በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም ከውሃ ማጠራቀሚያ (ታንከር) ውስጥ ውሃ እንደሚያገኙ ነዋሪዎቹ የተናገሩ ሲሆን አሁንም በተመሳሳይ መንገድ በቦቴ ተሽከርካሪ እየመጣ የውሃ ማጠራቀሚያው ውስጥ እንደሚደረግላቸው የገለጹት ነዋሪዎች ይህም ለሁሉም የሚበቃ እንዳልሆነ ያነሳሉ፡፡
አቶ ወንድማገኝ ታደሰ የ ነዋሪዎች ቅሬታ ልክ መሆኑን አምነው በከንቲባ ደረጃ በተቋቋመ ኮሚቴ የውሃ ፣የመብራት የመንገድ ባለሙያዎችን በማካተት ግንባታውን በተቻለ ፍጥነት ለመጨረስ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡



