አሁንም ብዙ ደም ፈላጊዎች እኛን እየተማጸኑ ነው-የኢትዮጵያ ደም እና ህብረህዋስ ባንክ አገልግሎት
ሐሙስ ጥቅምት 14 ቀን 2017(አዲስ ማለዳ)በተለያዩ ክልሎች እያጋጠመ ላለው የደም እጥረት የጸጥታ ጉዳይ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን የኢትዮጵያ ደም እና ህብረህዋስ ባንክ አገልግሎት የደም ለጋሾች ሀላፊ ሲስተር ሀና ለገሰ አስታውቀዋል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ከ300 እስከ 350 ዩኒት የሚሰበሰብ ቢሆንም በቀን ውስጥ ከሚያስፈልገው የደም አቅርቦት አንጻር አነስተኛ እንደሆነም ነው ሀላፊዋ የተናገሩት፡፡
በተለያዩ ክልሎች በተመሳሳይ መልኩ የደም አቅርቦት እጥረት እንደሚያጋጥም እና ከመንስኤዎቹ ውስጥ የጸጥታ ችግር ዋነኛው ሲሆን በማህበረሰቡ ውስጥ ያለው የግንዛቤ ማነስ እና የኑሮ ውድነት እንዲሁም የኢኮኖሚ ለውጥ እንደምክንያት ይነሳል ሲሉ ሲስተር ሀና ለገሰ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
ምንም እንኳን የደም ልገሳ ከአኗኗር ሁኔታ ጋር እንብዛም የሚያቆራኘው ነገር ባይኖርም በጎ ፍቃደኞች ለመለገስ በሚጠየቁበት ጊዜ “በዚህ ኑሮ ውድነት ምን በልተን ነው የምንለግሰው ” የሚል ምክንያት በብዛት እንደሚያጋጥማቸው ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም የማህበራዊ ግዴታ እና የሰው ህይወት የማዳን ሀላፊነት እንደመሆኑ መጠን ማንኛውም ሰው በፍቃደኝነት የጤና እክል ካላጋጠመው በስተቀር መለገስ እንዳለበት እና የኑሮ ውድነት ከደም ልገሳ ጋር የሚያያይዘው ነገር ሊኖረው እንደማይገባ ሀላፊዋ አስታውቀዋል፡፡
በሌላ መልኩ ለደም እጥረት መንስኤ ተብሎ የሚነሳው ደም ለገበያ ይውላ የሚል ሀሳብ እንዳለ እና እንደምክንያት ሊጠቀስ ይችላል ስትል አዲስ ማለዳ ጠይቃለች፡፡
ደም ያለምንም ክፍያ ከበጎ ፍቃደኞች የሚሰበሰብ እና በነጻ ለጤና ተቋማት የሚከፋፈል እንደሆነ እና ለተሰበሰበው ደም ምንም አይነት ክፍያ መጠየቅ ከህግ ውጪ የሆነ ድርጊት መሆኑን እና ለደም እጥረት እንደመንስኤ ሊነሳ እንደማይገባ የኢትዮጵያ ደም እና ህብረህዋስ ባንክ አገልግሎት የደም ለጋሾች ሀላፊ ሲስተር ሀና ለገሰ አመላክተዋል፡፡
በተጨማሪም ለአገልግሎቱ አሊያም አገልግሎት ላገኙበት ጓንት እና መርፌ ክፍያ ሊፈጸም እንደሚችል ነገር ግን ለደም ተብሎ ምንም አይነት ክፍያ እንደማይከፈል እና “ደም አይሸጥም አይለወጥም” ሲሉ አሳስበዋል፡፡



