ቅዳሜ ጥቅምት 23 ቀን 2017(አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ትናንት ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ባለስልጣንን ጨምሮ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸው ተነግሯል፡፡
የወጫሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ንጉሴ ኮሩን ጨምሮ ከ45 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ምንጮችን ዋቢ አድርጎ የዘገበው ቢቢሲ አመራሩና በርካታ የጸጥታ ሃይሎች መንግስት ኦነግ ሸኔ ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ሃይል ወደሚንቀሳቀስበት አካባቢ ሲያመሩ ግድያው መፈጸሙ ነው የተገለጸው።
የወረዳው አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ንጉሴ ኮሩ ከበርካታ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን የጸጥታ ችግር ወደተቀሰቀሰባት አካባቢው በማምራት ላይ እያሉ በታጣቂዎች ጥቃት እንደተፈጸመባቸውና የተኩስ ልውውጥ መደረጉን የገለጹት የአካባቢው ነዋሪዎች በጥቃቱ የተጎዱ ሰዎችም ወደ ሙከጡሪ ሆስፒታል ለህክምና እርዳ መሄዳቸው ተነግሯል ።
የሰሜን ሸዋ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት በበኩሉ አቶ ንጉሡ ኮሩ “ለሕዝባቸው ብልጽግና ቀን ተሌት ይሰሩ የነበሩ” መሆናቸውን ገልጾ የሐዘን መግለጫ አውጥቷል።
መግለጫው አክሎም በወጫሌ ወረዳ ካራ በሚባል አካባቢ የጸጥታውን ሁኔታ ለመከታተል ተሰማርተው ባሉበት መንግሥት ሸኔ ሲል በሚጠራቸው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች መገደላቸውን ገልጿል።



