የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አሁን ያለበትን ዋና ጽ/ቤት በመልቀቅ አዲስ ቢሮ እንዲሰጠው ለኪራይ ቤቶች አስተዳደር ማመልከቻ አስገባ፡፡
የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደገለጹት ፓርቲው በበቅሎ ቤት የሚገኘውን ዋና ጽ/ቤቱን ጨምሮ ሌሎች ጽ/ቤቶቹን ለቆ አዲስ ሕንፃ ውስጥ እንዲገባ አማራጮችን እየተመለከተ ነው፡፡
የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ናትናኤል ፈለቀ ግን ‹‹ ቢሮ እየለቀቅን አይደለም፤ አሁን ያሉን ቢሮዎች ሦስት የተለያዩ ቦታዎች ላይ ተበታትነው የሚገኙ በመሆናቸው እና ፓርቲው አሁን ከሚፈልገው የቢሮ ፍላጎት አንጻር በቂ ሆነው ስላላገኛቸው ለኪራይ ቤቶች ማመልከቻ አስገብተናል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ኢዜማ ሲገለገልባቸው የነበሩ የፓርቲው ጽህፈት ቤቶች እንዲመለሱለት ሲጠይቅ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ አዲስ አበባ ስቴዲዮም፣ በቅሎ ቤት እና ባሕር ዳር የሚገኙ ጽ/ቤቶቹን ያለአግባብ ኢዜማ ወስዶ እየተገለገለባቸው ነበር የሚሉት የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ አዳነ ታደሰ ናቸው፡፡
‹‹የቀድሞ የኢዴፓ የአሁኑ የኢዜማ አራት አመራሮች ከደንብ እና መተዳደሪያችን ውጪ የባንክ ሂሳባችን ውስጥ ተቀምጦ የነበረውን ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ብር በሕገ ወጥ መንገድ ወስደውታል፡፡ ይህንን ለማስመለስ ከባንኩ የአስተዳደር ሠራተኞች ጋር ለመነጋገር ኮሚቴ አዋቅረናል፤ ይህ ካልሆነ ግን ነገሩን የምንፈታው ወደ ክስ በማምራት ብቻ ይሆናል›› ሲሉ አዳነ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱን ሲያብራሩ ደግሞ ‹‹ኢዜማ ገና ሕጋዊ እውቅና ስለሌለው ወደ ክስ ልናመራ አንችልም ስለዚህም የመጀመሪያው እርምጃችን ባንኩን እና የኢዜማ አመራሮችን ማነጋገር ይሆናል፤ ነገር ግን ይህ ለውጥ ካለመጣ ወደ ሕግ እናመራለን›› ብለዋል፡፡
ናትናኤል በበኩላቸው ‹‹አንደ አገር አቀፍ ፓርቲ ለመመዝገብ የሚያስፈልገውን ሙሉ መስፈርት አሟልተን አስገብተናል የምስክር ወረቀት እስኪሰጠንም እንደ ማንኛውም ፓርቲ ለመንቀሳቀስ የሚረዳንን የቅድመ እውቅና ደብዳቤ ቦርዱ ስለጻፈልን እስከ አሁንም የምንቀሳቀሰው በዚህ ደብዳቤ ነው፣ እና ኪራይም ስንከፍል ነበር›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
ከኢዜማ ጋር የነበረንን ያለመግባባት በንግግር ለመፍታት እየሞከርን ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ‹‹ኢዜማ ግን አዲስ ቢሮ እያፈላለገ ስለመሆኑም ይሁን ስለማግኘቱ ምንም የሰማነው ነገር ባይኖርም አሁንም ቢሆን ግን ቢሮዎቻችን እንዲመለሱልን ነው የምንፈልገው፤ ለዚህም ጥረት እያደረግን ነው›› ብለዋል፡፡ ከባንክ አካውንታችን ገንዘብ ተወስዶብናል ለሚለው ወቀሳም ‹‹ በሕግ የተያዘ ጉዳይ በመሆኑ አስተያየት ለመስጠት እቸገራለሁ›› ሲሉ ናትናኤል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡
አዳነ ‹‹የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ከ1992 ጀምሮ ያከራየን ለኛ ነው አሁንም ድረስ ክፍያዎች የሚፈጸሙት በኢዴፓ ስም ነው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሁንም ንብረቱን ባለቤቶች እኛ ስለሆንን ሊመለስልን ይገባል›› ብለዋል፡፡ አዲስ ማለዳም ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ እዳ የኪራይ ቤቶች መጠየቁን እና ፓርቲአቸውም ይህንን ለመክፈል ተዘጋጅቶ እንደሆን ላቀረበችላቸው ጥያቄ መልስ ባይሰጡም ምንአልባት በባንክ አካውንታቸው ውስጥ ያለው ገንዘብ ከተመለሰ ሊከፍሉ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
ከቢሮዎቹ ጋር በተያያዘ የሚኖሩ እዳዎች ለመክፈልም በቅድሚያ ኢዴፓ ያለመክሰሙን ተከትሎ ከምርጫ ቦርድ ምንም ዓይነት እገዳ እንደሌለበት ካረጋገጠ በኋላ አስቸኳይ ስብሰባውን በማድረግ አዳነ ታደሰን በፕሬዝዳንትነት፣ ፅጌ ጥበቡን በምክትል ፕሬዝዳንትነት መሾሙ ይታወሳል፡፡
ኢዜማ በበኩሉ በሕገወጥ መንገድ የያዘው ምንም ዓይነት ንብረት እንደሌለና የኢዴፓን ፓርቲ ቢሮ እየተጠቀመ ያለው ግን የኢዴፓ ጠቅላላ ጉባኤ ፓርቲውን ሲያከስም የያዘው ቃለ ጉባኤ ላይ ንብረቶቹን ለማን እንደሚያስረክብ ሲገልጽ አዲስ ለሚመሰረተው ፓርቲ እንዲገለገልበት መወሰኑን ተከትሎ መሆኑን እንጂ የሕግ ጥሰት ፈፅሞ አለመሆኑን ከዚህ ቀደም የፓርቲው ሕዝብ ግንኙነት ናትናኤል ፈለቀ ለአዲስ ዘመን መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ከወራት በፊት ግንቦት 1 እና 2/2011 በተደረገ የመስራቶች ጉባኤ ግንቦት 7ን፣ ኢዴፓን፣ ሰማያዊ ፓርቲን፣ የቀድሞ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህን (አንድነት) ጨምሮ በኋላ በሂደትም የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) እና የከንባታ ሕዝብ ኮንግረስ (ኮሕኮ) ራሳቸውን በማክሰም በግለሰብ ደረጃ ተመዝግበው አዲስ ፓርቲ መመሰረታቸው አይዘነጋም፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 64 ጥር 16 2012



