ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ የሆነ እና በወንጀል ድርጊት የጠገኘ ሃብትን የሚያስመልስ በመርማሪ ፖሊሶች፣ በዐቃቤአን ሕግ፣ በሃብት ጥናት ባለሞያዎች፣ በፋይናንስ መርማሪዎች እና በኢንጂነሮች የተዋቀረ አዲስ ዳይሬክቶሬት ወደ ሥራ ገባ።
ከአንድ ዓመት በላይ ይህንን ሥራ ሲሠራ የነበረውን ግብረ ኃይል ወደ መደበኛው አሰራር በማስገባት የተዋቀረው ይህ ዳይሬክቶሬት ከተለያዩ አገራት ልምዶችን በመቅሰም መዋቀሩን አዲስ የተሾሙት እና በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕግ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አለምአንተ አግደው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ግብረ ኃይሉ ባለፈው አንድ ዓመት ቀላል የማይባል ሃብት ቢያስመልስም በባለቤትነት ሥራውን የሚከታተል አካል ባለመኖሩ የተወሰኑ ክፍተቶች እንደነበሩ ኃላፊው ተናግረዋል። የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም በዘርፉ ላይ ባጠናው ጥናት በኤጀንሲ ደረጃ እንዲቋቋም አስተያየት መስጠታቸውንም ጨምረው ጠቅሰዋል።
‹‹በመደበኛ ሥራ ተይዞ የሃብት ማስመለስ ሥራን እንደ ሁለተኛ ሥራ መቁጠር እና ዐቃቤአን ሕግም እስከዛሬ ባለው ልምድ መሰረት ጥፋተኞችን በወንጀል በማስጠየቅ ላይ ማተኮራቸው ውጤቱ ላይ የራሱ ጫና ነበረው›› ሲሉ ተናግረዋል። ‹‹የወንጀል ሕግ ኹለት አላማዎች አሉት፣ አንዱ ለሌሎች መቀጣጫ ማድረግ እና ራሱ ወንጀለኛው ዳግም ወንጀል እንዳይሠራ መቅጣት እንዲሁም በወንጀል በተገኘ ሃብት መበልፀግ እንዳይቻል ማድረግ ነው፣ ይህም ቡድን የተቋቋመው ይህንን ለማሳካት ነው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የወንጀል ሥራ ክትትሉ እና በፍርድ ቤትም ክስ መስርቶ ማስቀጣቱ እንዳለ ሆኖ ይህ ዳይሬክቶሬት ግን በምዝበራ የተገኘውን ሃብት በመከታተል እና ምንጩን ለይቶ መመለስ ላይ ብቻ ያተኩራል። በኬኒያ እና በደቡብ አፍሪካ ይህ ክፍል ራሱን ችሎ በኤጀንሲ ደረጃ የተዋቀረ ሲሆን በእኛ አገር ግን እስከዛሬ በተናጠል ሲሠራ የነበረ ሥራ መሆኑን ይናገራሉ።
የፋይናንስ ደህንነት ተቋሙም የሚሰበስበው የደህንነት ስጋት ጠቋሚ መረጃ ሲኖረው በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለተቋቋመው ለዚህ ቡድን የሚያሳውቅ ሲሆን ፖሊስ የወንጀል ድርጊቱን መከታተሉን ይቀጥላል፤ ሃብቱን በፍትሃ ብሄርም ሆነ በወንጀል የማስመለስ ሂደቱን ግን ይህ ዳይሬክቶሬት የሚመራው ይሆናል እንደ አለም አንተ ገለፃ።
በወንጀል የተገኘ ገንዘብን ለማስመለስ አንዱ አስቸጋሪ የነበረው የሕግ ማዕቀፎች ሲሆኑ እነዚህንም ለማሻሻል ሥራዎች እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
በተለይም ከሙስና ወንጀሎች፣ የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ከከባድ ማታለል፣ ከአደንዛዥ እፅ ዝውውር እንዲሁም ከግብር ስወራ የሚገኝ ሃብትን ማስመለስ የአዲሱ ዳይሬክቶሬት ዋነኛ ትኩረቶች እንደሚሆኑ አለምአንተ ጨምረው ገለፀዋል።
ከሰኔ እስከ ሕዳር ባሉት አምስት ወራት ያለአግባብ የተመዘበረ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ወደ መንግሥት ካዝና በጥሬ ገንዘብ ማስመለስ መቻሉን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
‹‹የሃብት ጥናት፣ ማሳገድ፣ ምርመራ እና ማስተዳደር በሚል በፌዴራል ፖሊስ ውስጥ ያለውን መዋቅር ሥራ የሚወስድ እና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያለውን የምርመራ መዝገቦች የመምራት ሥራን ሙሉ ለሙሉ ጠቅልሎ ወደ መውሰድ የሚቀይር ተግባር ነው›› ሲሉ የአዲስ ማለዳ የፌዴራል ፖሊስ ምንጭ ይጠቅሳሉ። ‹‹ይህም ውሳኔ በፌዴራል ፖሊስ ውስጥ ውዝግብ ማስነሳቱንም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
አዲስ ማለዳም በፌዴራል ፖሊስ ቅሬታ ያስነሳውን የሥራ ክፍል የሚቆጣጠሩትን የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ተኮላ አይፎክሩን አግኝታ ለማነጋገር ብትሞክርም ለሥራ ከአገር ውጪ በመሆናቸው ሃሳባቸውን ማካተት ሳትችል ቀርታለች።
ቅጽ 2 ቁጥር 64 ጥር 16 2012



