የጠፉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የመከላከያ ሰራዊት እያፈላለገ ነው

በተለያየ ግዜ መጥፋታቸውን ቤተሰቦቻቸው ያስታወቁትን ስምንት ተማሪዎችን ጨምሮ ባጠቃላይ 19 ሰዎችን የመከላከያ ሰራዊት በማፈላለግ ላይ እንደሆነ በሰራዊቱ ያሉ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ተናገሩ።

ከደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ጠፍተዋል የተባሉትን የተማሪዎች ዝርዝር በመውሰድ 14 ተማሪዎች እስከ አሁን ያሉበት ባለመታወቁ እና የስምንቱ ተማሪዎች ቤተሰብም መጥፋታቸውን በማመልከቱ ፍለጋው ተጠናክሮ መቀጠሉን አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።

አዲስ ማለዳ እጅ የገባው የፌደራል ፖሊስ የስም ዝርዝር አንደሚያሳየው የምርመራው መሰረት የሆነው በማህበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር የነበረው የ 17 ተማሪዎች የስም ዝርዝር ነው። ይሄው ዝርዝር እንደሚያሳየው ግን 11 ተማሪዎች ወላጅ ጠፍተውብኛል ሲል ጥያቄ አቅርቦባቸዋል። ግርማቸው ሃብቴ፣ ጤናለም ሙላቴ፣ ሙሉ ዘውድ፣ ሞናሞን በላይ፣ ቢተውልኝ አጥናፉ፣ ሳምራዊት ቀሬ፣ ግርማነሽ የኔነህ እና ሌሎች ሶስት ተማሪዎች ያሉበት ዝርዝር ቤተሰብ ያመለከተባቸው ሆነው ተገኝተዋል።

አታለለኝ ጌትነት፣ ትእግስት መሳይ፣ ክንደዬ ሞላ፣ ዘመድ ብርሃን እና መሰረት ከፍ ያለው በማህበራዊ ሚዲያ ስማቸው ቢዘዋወርም በዩኒቨርሲቲው ወይም በፈተናዎች ድርጅት የመረጃ ቋቶች ውስጥ ሊገኙ ያልቻሉ ናቸው ተብለው በዝርዝሩ ላይ ሰፍረዋል።

የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስቴር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እንዳሉት ይህ ፍለጋ የ2012 የትምህርት ዘመን ብቻ ሳይሆን ወደ ኋላ በመሄድም ጭምር የተደረገ ሲሆን የተባሉትን ተማሪዎች ግን ማግኘት አልተቻለም። የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሪታሪያት ሃላፊ ንጉሡ ጥላሁን እንደገለፁት ከሆነ አነዚህ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲዎች የስም ዝርዝር ውስጥ ባይገኙም ፍለጋው ግን ቀጥላል።

በተጨማሪም ተመሳሳይ ሰነድ እንደሚያሳየው ከእገታው ያመለጠችው አስምራ ሹምዬ፣ ከልጃቸው ጋር አብረው ተይዘው ጉዳትም ደርሶባቸው የነበሩት አባት እና ሌሎች አምስት ሰዎች ትኩረት ይፈልጋሉ በሚል ተለይተዋል።

በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት የመጀመሪያዋ ጠቋሚ አስምራ የምትሰጠው ቁጥር እና የስም ዝርዝር ትክክል እንዳልሆነ ለዚህም በታህሳስ 26/2012 በቄለም ወለጋ ዞን ለሚገኝ የኮማንድ ፖስት በፊርማዋ እና በምስክር ፊት አረጋግጣ የሰጠችው የስም ዝርዝር አምስት ሰዎች መጥፋታቸውን ብትገልጽም ኋላ ላይ ግን ቁጥሩን ከፍ በማድረጓ ጥርጣሬ መኖሩን ሃላፊዎቹ ገልፀዋል።

‹‹ልጅቷ የታገተችው ከደንቢ ዶሎ ወደ ጋምቤላ በሚወስደው መንገድ ላይ ቢሆንም፣ በሌላ አቅጣጫ ሲጓዙ የጠፉትን ጨምራ ለመገናኛ ብዙሃን ገልፃለች›› ሲሉ ንጉሡ  ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹የኢንጂነሪንግ ተማሪ ነኝ ነው ያለችው ነገር ግን በዚህ አመት ምንም አይነት አዲስ የኢንጂነሪንግ ተማሪ ወደ ዩኒቨርሲቲ አልተመደበም፤ ስለዚህ ብዙ የሚጋጭ ነገር ነው የተናገረቸው›› ሲሉ ጥርጣሬዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳም ወደ አስምራ በተደጋጋሚ የስልክ ጥሪዎችን ብታደርግም አስምራ ወደ ሌላ አገር መሄዷን እና ስልኳንም ለመስጠት ፈቃደኛ ያለመሆናቸውን የእጅ ስልኳን የያዙት እና ጎረቤቶቿ መሆናቸውን የተናገሩ ግለሰቦች ተናግረዋል።

ወደ ደንቢ ዶሎ የተጓዘው እና በሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል የተመራው ቡድን በዩኒቨርሲቲው ከእገታ ተመልሰው ከነበሩ ተማሪዎች አንድም ተማሪ ያለማግኘታቸውን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች። ንጉሡም ‹‹በግቢው ውስጥ አንድም የአማራ ክልል ተማሪ የለም፣ ከእነዚህ ውስጥ ግን የታገተ ሊኖር ይችላል፣ ደንቢ ዶሎ ያለ ሊኖር ይችላል፣ አዲስ አበባ ያለ ሊኖር ይችላል፤ ይሄንን ለግዜው አናውቅም›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የመከላከያ ሰራዊት ምንጮች እንደሚሉትም የሰራዊቱ አባላት 21 ተማሪዎችን በታገቱ በአራት ቀን ውስጥ ከአጋቾች አስፈትቶ ወደ ዩኒቨርሲቲው መመለሱን ይናገራሉ።

‹‹የአገር ሽማግሌዎች ባደረጉት ጥረት በጣም በቀላሉ ነበር ተለቀው ወደ ዩኒቨርሲተ የተመለሱት፣ በእገታ የቆዩትም ጥቂት ቀን ስለሆነ ያለ ምንም ጉዳት እና ችግር ተመልሰው ነበር›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ‹‹ከዛ በኋላ ግን ምን አልባት በፍርሃት ተመልሰው ሊወጡ እንደሚችሉ እንገምታለን፤ የሰራዊቱ አባላት ግን አሁንም በየጫካው እስከ ድንበር ድረስ አሰሳ እያደረጉ ነው›› ሲሉ አብራርተዋል።

የመከላከያ ሰራዊት ከ አራት አመት በላይ በአራቱም የወለጋ ዞኖች ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ ሆነው የቆዩ አካባቢዎችን ወደ መንግስት ቁጥጥር ስር  ማስገባቱን፣ የቀሩ የሸኔ ታጣቂ አባላትም ወደ ድንበር አካባቢዎች አንዲሁም በጣም ጥቂቱ ደግሞ ወደ ጥቅጥቅ ደን መግባቱን እና አሁንም በየቀኑ የሚማረኩ ሽፍታዎች እንዳሉ አክለዋል።

‹‹ለረጅም ግዜ አገልግሎት መስጠት አቁመው የነበሩ ዋና ዋና መንገዶችን ጨምሮ የተለያዩ አካባቢዎችን ወደ መንግስት ቁጥጥር ሰራዊቱ አስገብቷል፣ ምንም እንኳን አሁንም አንዳንድ አካባቢዎች የሰራዊት አጀብ ቢጠይቅም እንደልብ ለመንቀሰቀስ ተችሏል›› ሲሉም ምንጫችን ይናገራሉ።

ባጠቃላይም በመጀመሪያ ታግተው የነበሩ እና በሰራዊቱ የተመለሱ 21 ሰዎች፣ በማህበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወሩ የነበሩ 17 ሰዎች፣ ሁለት በቤተሰብ ጥቆማ የመጡ ሰዎችና ስድስት በአንድ ታጋች አባት ጥቆማ የመጡ፤ ባጠቃላይ 46 የስም ዝርዝር ለምርመራ ጠረጴዛ ላይ ቀርቧል። ከዚህም ውስጥ 19 ሰዎች የተለያዩ የቴክኒክ ምርመራዎች ተደርገው የተለዩ ሲሆን እነዚህን መንግሰት እንደሚያፈላልግ ቃል ገልቷል። ከእነዚህም 14ቱ የመጥፋት ማመልከቻ የቀረበባቸው በመሆናቸው እየተፈለጉ መሆኑ ተገለጿል።

ለዚህም የቴክኒክ ቡድን የተቋቋመ ሲሆን ይህ ቡድን ወደ አካባቢው ተጉዞ ሁለት ግዜ ሪፖረት ማቅረቡን ንጉሡ ተናግረዋል።

ወደ አዲስ አበባ ተጠርተው የመጡት እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) እንዲሁም ከተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር የተወያዩት የሞንሞን አባት እንደገለፁት ‹‹ደህና ናቸው እናመጣቸዋልን ብለውናል›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋ። የውዴ ግርማው አባትም ወደ አዲስ አበባ እንዳልመጡ ነገር ግን በወረዳ ተብሎ አንድ ሌላ ልጅ የጠፋባቸው የአካባቢው ሰው ተወክለው አዲስ አበባ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የሶስተኛ አመት የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነው የግርማው ሃብቴ ወንድም እንደሚሉት የእጅ ስልካቸው የቴሌኮም አገልግሎት እስኪቋረጥ ድረስ ይጠራ እንደነበር ይናገራሉ። ‹‹ከተያዙ ጀምሮ ቢያንስ እስከ አንድ ወር ድረስ ይጠራል ግን አይነሳም ነበር፣ አሁን ምንም የለም፤ አባቴ አዲስ አበባ ሄዷል ምን እንዳሉት ግን አላውቅም›› ሲል ገልጿል።

አዲስ ማለዳ በመከላከያ ሰራዊት ካሉ ታማኝ ምንጮቿ መረዳት እንደቻለችው የጠፉትን 19 ልጆች የማፈላለጉ ስራ ከቄለም ወለጋ ባለፈ እስከ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ድረስ እንደሚዘልቅ ተናግረዋል፡፡ ሰራዊቱ ምን አልባት የጠፉትን ልጆች ወደ ድንበር እና ወደ ጎረቤት አገሮች የማሸሽ አዝማማያ ሊኖር ይችላል በሚል ጥርጣሬ አሰሳ እያከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here