እንደ አዲስ ከተዋቀረ አንድ ዓመት የሞላው የሰላም ሚኒስቴር ስር የሚገኘው የክልሎችና አርብቶ አደር አካባቢ ድጋፍ ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት፣ በድጎማ እንዲያከፋፍል የተሰጠውን 450 ሚሊዮን ብር የመዋቅር ሥራውን ባለማጠናቀቁ ምክንያት ማከፋፈል አልቻለም።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአዋጅ ከተሰጡት ሥልጣኖች መካከል የሆኑት የፌዴራሊዝም እና አርብቶ አደር ጉዳዮች ዘርፍ ሲሆኑ፣ በዚህም መሰረት ለአራት ክልሎች በድጎማ እንዲያከፋፍል በገንዘብ ሚኒሰቴር ገንዘቡ ተሰጥቶታል። ሆኖም ለስድስት ወራት ሳያከፋፍል ቀርቷል።
ለዚህም እንደ በምክንያትነት የተጠቀሰው በየክልሉ የነበረው የአርብቶ አደር ቢሮዎች መዋቅር በኩል ጉዳይ ሲሆን፣ ተቋሙ ገንዘቡን በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ እያዋለ አይደለም በሚል በአዲስ መዋቅር እንዲተካ ቢወሰንም ይህንን ግን በተባለው ጊዜ ውስጥ ማካሄድ አልተቻለም። የሶማሌ፣ አፋር፣ የደቡብን አርብቶ አደር እና የኦሮሚያ ክልሎች ድጎማውን የሚያገኙት ክልሎች ናቸው።
በሰላም ሚኒስቴር የአርብቶ አደር ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ ወንድማገኝ ኃይሌ፣ ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር ድጋፉ ይደርስ የነበረው አርብቶ አደሮችን ብቻ ትኩረት አድርጎ እንደነበር ይገልፃሉ። በአንጻሩ አሁን ድጋፉ አርሶ አደሩን ጨምሮ በግብርናው ዘርፍ ለሁሉም እንዲደርስ በመታሰቡ እና ሁሉንም አካታች የድጋፍ እቅድ በመታቀዱ ሥራውን ሰፊ አድርጎታል። በአዲሱ አተገባበርም በስድስቱ ክልሎች የተለያዩ የፕሮጀክት መሥርያ ቤቶችን በመክፈት እና በመሥርያ ቤቶቹ የክልሎቹን ባለሙያዎች በማሳተፍ ለአርብቶ አደሮቹ እና አርሶ አደሮቹ ድጋፉ ይደርሳል ተብሎ እየተጠበቀ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው ይህ አዲስ የድጎማ መዋቅር እስኪፀድቅ እየተጠበቀ መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊው፣ እንደፀደቀም ወደ ሥራ እንደሚገቡ ተናግረዋል። ይህንን መዋቅር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ለብቻው ለመዘርጋት ሥልጣኑ እንደሌለውም ገልፀዋል። አሰራሩንም ለመቀየር የ 2011 በጀት ዓመት ኹለተኛው ግማሽ ዓመት ላይ በተደረገ ግምገማ አሠራሩ ለውጥ ያለማምጣቱ እንደሆነ ገልፀዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የልዩ ድጋፉ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል የኦሮሚያ ክልል አርብቶ አደሮች ሲሆኑ፣ ነገር ግን የዚህ ዓመት የልዩ ድጋፍ ገንዘቡ ባለመድረሱ ምክንያት መሠራት እያለባቸው በበጀት እጥረት ምክንያት ያልተሠሩ ሥራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። አያይዘውም በግብርና በኩል ያሉ መደበኛ ፕሮግራሞች ሲኖሩ ለነሱ መደገፊያ ነበር በጀቱን እናውለው የነበረው ብለዋል።
‹‹ውሃ ላይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው፣ ግጦሽን በተመለከተ በተጨማሪም የከብቶች መኖን ጨምሮ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ላይ አብዛኛውን መደበኛ ከምናገኘው በጀት ውጪ ድጋፉ የሚውልባቸው ነገሮች ነበሩ›› ያሉት የኦሮሚያ እርሻ እና ተፈጥሮ ሃብት ምክትል ቢሮ ኃላፊ እንዳልካቸው ተፈሪ ናቸው።
ልዩ ድጋፍ የሚሹ በኦሮሚያ ክልል 10 ዞኖች ላይ ያሉት አርብቶ አደር መገኛዎች በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቁ ቦታዎች ነበሩ። ነገር ግን ያንን ድርቅ ለመቋቋም በበጀቱ እጥረት ምክንያት የተሠራ ነገር ባለመኖሩ ጉዳቱን ከባድ እያደረገው ይገኛል ሲሉም እንዳልካቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 65 ጥር 23 2012



