በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የአንበጣ መንጋ ዳግም መከሰቱን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ገለፀ።
የአንበጣ መንጋው ከዓርብ ጥር 29/2012 ምሽት ጀምሮ ከአማራ ክልል አጎራባች አካባቢዎች ወደ ክልሉ ደቡባዊ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች መግባቱን በቢሮው የፀረ ተባዮች ዳይሬክተር አቶ መብራህቶም ገብረኪዳን መናገራቸውን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘግቧል።
መብራህቶም የአንበጣ መንጋው በመስኖ በለሙ ሰብሎችና በእንስሳት መኖ እንዲሁም ዛፎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል በመግለፅ የአንበጣ መንጋ መከሰቱን የሚያመላክት መረጃ ለሁሉም የማዳረስ ስራ እንደተሰራ ነው ብለዋል።
መንጋው ጉዳት ከማድረሱ በፊት ለመከላከል እና ከአካባቢው ለማጥፋት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ያስረዱ ሲሆን መንጋውን በአጭር ጊዜ ለማጥፋት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከዚህ ቀደም ያሳየውን የተቀናጀ ተሳትፎ በመድገም እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።



