የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ መንግሥት ድጎማ በማድረግ ከውጪ እያስገባ ለኅብረተሰቡ ሲያሰራጭ የነበረው ፓልም የምግብ ዘይት የጥራት ደረጃ መሻሻሉን አስታወቀ።
ፓልም የምግብ ዘይት መንግሥት የዋጋ፣ የአቅርቦት እና የስርጭት ቁጥጥር እያደረገባቸው ከሚገኙ መሠረታዊ ሸቀጦች መካከል ተጠቃሽ ነው። ሆኖም ዘይቱ በውስጡ ካለው የስብ መጠን እና ከአስመጪዎች መረጣ ፍትሐዊነት ጋር ተያይዞ ቅሬታዎች ሲነሱ እንደነበር ይታወቃል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎችና ውዝግቦችን ለመፍታት የምግብ ዘይት አቅርቦትና ስርጭት ማስፈጸሚያ መመሪያ ቁጥር 020/2011 አውጥቶ ከታኅሳስ ወር 2012 ጀምሮ ተግባራዊ አድርጓል። በዚህ መሰረት ከዚህ በፊት ሲቀርብ የነበረው የፓልም የምግብ ዘይት ወይም በተለምዶ የሚረጋው ዘይት ሳይሆን ፓልም ኦሊን (palm olien) የተባለ ፈሳሽ የምግብ ዘይት መሆኑ በመመሪያው መቀመጡ ተገልጿል።
በፊት ይቀርብ የነበረው ፓልም የምግብ ዘይት የጥራት ደረጃ CES138:2015 የነበረ ሲሆን፣ አሁን የሚቀርበው ፓልም ኦሊን የምግብ ዘይት ተሻሽሎ CES245 የጥራት ደረጃ መስፈርቶችን አሟልቶ የተመረተና በቫይታሚን ኤ እና ዲ የበለጸገ መሆን እንደሚገባው ተገልጿል።
መመሪያው ከጥራት ደረጃ በተጨማሪ የዘይት አስመጪዎች ምልመላ፣ የዋጋ ትመና እና የትርፍ ምጣኔ አወሳሰንን የያዘ ነው ተብሏል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ አቅራቢዎችን ለመመልመል በወጣው መስፈርት መሰረት በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች ደረጃ በሚመለከታቸው የዘርፉ አካላት አማካኝነት አሳታፊ በሆነና ግልጽነት ባለው መልኩ 24 የምግብ ዘይት አስመጪዎች ተመርጠው ወደ ሥራ መግባታቸው ተገልጿል።
በሌላም በኩል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስገዳጅ የኢትዮጵያ የጥራት ደረጃ የወጣላቸው የገቢ ምርቶች ላይ ባደረገው የቁጥጥር ሥራ፣ ከጥራት ደረጃ በታች የሆነ 19 ሺሕ 770 ጀሪካን ፓልም የምግብ ዘይት ወደ አገር ውስጥ ሊገባ ሲል መታገዱን አስታውቋል።
የቁጥጥር ሥራው ከፓልም የምግብ ዘይት በተጨማሪ የቤት ክዳን ቆርቆሮ፣ የአርማታ ብረት፣ ሳሙና፣ ሚስማር እና የታሸጉ ምግቦች ላይ መከናወኑ ተገልጿል።
ቅጽ 2 ቁጥር 67 የካቲት 7 2012



