ቫላንታይንን በኮሮና ቫይረስ ስጋት መካከል

0
916

ከዚህ ቀደም በነበሩት ዓመታት አዲሰ አበባ እንዲሁም የተለያዩ ከተሞች የፍቅረኞችን ቀን ለማክበር ደፋ ቀና ይሉ ነበር። የተለያዩ ሆቴሎች እና ሬስቶራንቶች የተለያዩ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት በዓሉን ያደምቁታል። ምንም እንኳን የፍቅረኞች ቀን መከበር ‹አለበት የለበትም› የሚለው ሐሳብ አሁንም ድረሰ አከራካሪና አጨቃጫቂ ቢሆንም፤ ቀይ ልብሶችን የለበሱ ጥንዶችን በብዛት ማየትና እነርሱን ለማተናገድ ሽር ጉድ የሚሉ ደጋሾችን ማስተዋል ተለምዷል።

ዘንድሮ ከወር በፊት ኮሮና ቫይረስ ተከስቷል። በቅርቡ እንደተመለከትነውም ከሆነ ቫይረሱ ለዓለም ስጋት በመሆኑ ጋብቻቸውን የፈፀሙ ጥኝዶች ሳይቀሩ አፋቸውን በጭንብል እንዲሸፈኑ ተገድደውም ነበር።

ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ አይግባ እንጂ በተለይም ቻይና በቫይረሱ መጠቃቷ፣ የኢትዮጵያን ነጋዴዎች ገበያ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እንዲቀዝቅዝ አድርጓል። ለዚህ ማሳያ ደግሞ ለወትሮው በቀይ አልባሳት፣ ጌጣጌጥና መዋቢያዎች ደምቀው የሚታዩት የአዲሰ አበባ የአበባ መሸጫ መደብሮች፣ ቡቲኮችና ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች ነው። ይህም ቀኑን ባናስበው እንኳን እንድናስታውሰው ያስገድድ ነበር።

የዘንድሮ በተለይም እስከ ዋዜማው ዕለት ድረስ መደብሮቹ እንደ ከዚህ ቀደሙ በቀይ አልባሳት አልደመቁም። እንደውም ፈዘው መታየታቸውና የተለመዱ አልባሳቶችን የሚሸጡ መደብሮች እንኳን ምርቶችን ሞልተው አለመታየታቸው፣ ‹‹ምን ገጥሟቸው ነው?›› የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል።

ይህንን ጥያቄ አዲስ ማለዳ ማንሳቷ አልቀረም። የዘንድሮውን ቫላንታይን ወይም የፍቅረኞች ቀንን በተመከለተም የተለያዩ ቦታዎች ጎራ ብላ ስለ ቀኑ፣ ስለ ገበያው እና ሌሎችን ጉዳዮች አስመልክቶ የተለያዩ ሰዎችን አናግራለች።

በቦሌ አካባቢ በሚገኝ አንድ ቡቲክ ውስጥ ነው፤ መደብሯን ስታጸዳ ያገኘኛት። ሥሜ አይጠቀስ ያለችው ሴት፣ ስለ ገበያው ሁኔታ ከአዲስ ማለዳ ለቀረበላት ጥያቄ ‹‹የዘንድሮው ቫላንታይን የቀዘቀዘ ነው።›› ብላለች። ‹‹ገበያም የለንም፣ ከዚህ በፊት በነበሩት ዓመታት ወንዶች ለፍቅረኞቻቸው ስጦታ ለማሰጠት ልብስ ይገዙን ነበር። ሴቶቹም ቢሆኑ አምረውና ደምቀው በዓላቸውን ለማክበር ልብስ፣ ጫማ እና ሌሎችንም ጌጣጌጦች ይገዙ ነበር›› ስትልም ታስታውሳለች።

‹‹ይሁን እንጂ የዘንሮው ደግሞ የተለየ ነው። ገበያ የለንም። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የተለያዩ ምርቶችን የሚያስመጡ ነጋዴዎች ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ፍራቻ ስላላቸው ወደ ቻይና ለመሄድ ፍላጎት ስለሌላቸው ነው›› ስትል ታስረዳለች።

ሪታ የአበባ እና ዲኮር መደብር የሚገኘው ደንበል አካባቢ ነው። በመደብሩ ውስጥ አበባዎችን በማዘጋጀት ያገኘናት ኤልሳ ብሩ ‹‹የፍቅረኞች ቀን እንደዚህ ቀዝቀዞ አይቼው አላውቅም፤ የአበባ እጥረትም አለብን። ከሰሞኑን አንድ ቀይ አበባ 3 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን እስከ 15 ብር እየተሸጠ ነው›› ብላለች።
ይህም ብቻ ሳይሆን ምክንያቱን ባታውቅም ብዙ ገዢዎችም እንደማይመጡ በመግለፅ፣ በመደብሩ ውስጥ ለዕለቱ ይሆናል ያሏዋቸውን እንደ ቀይ አበባ፣ ፖስት ካርድ፣ ሻማ የአገር ውስጥና የውጭ ማዘጋጀታቸውን ነው የምትናገረው።

ኤልሳ ተከስተ በመርካቶ አካባቢ የሴቶች መዋቢያ ምርቶችን አቅራቢ ነጋዴ ናት። ‹‹ቀደም ባሉት ዓመታት ከሳምንት በፊት ነበር ወንዶችም ይሁኑ ሴቶች ለፍቅረኞች ስጦታ ለመስጠት ጠይቀው ይገዙንም ነበር። አሁን አይደለም የሚገዛ የሚጠይቁንም የሉም ማለት ይቻላል›› ስትል ታስረዳለች።

መለሰ የተባለው የአበባ እና ጌጣጌጥ ነጋዴ በበኩሉ እንዲህ ይላል፤ ‹‹እስከ አሁን ብዙ አበባ አላመጣሁም። ዋጋውም ጨምሯል። ጠያቂም የለም። ለዚህም ምክንያቱ የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ሊሆን ይችላል።›› ሲል ያስረዳል።

የአበባ፣ የስጦታ እና ዲኮር መደብር ነጋዴዎቹ ለፍቅረኞች ቀን የሚሆኑ ፖስት ካርዶችን ከ 10 ብር ጀምሮ እስከ 50 ብር፣ የአገር ውስጥ ሻማ ከ35 ብር እስከ 250 ብር፣ እንዲሁም አንድ አበባ እስከ 10 ብር እንደሚሸጡ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ስለ ፍቅረኞች ቀን – ሰዎች ምን ይላሉ?
ከነጋዴዎቹ መካከል አስተያየት የሰጡት ሰው ይህን ብለዋል፤ ‹‹እኔ አሁን ባለትዳር ነኝ። ቢሆንም ከማግባቴ በፊት ቀኑን አክብሬያለሁ። ደስ የሚል ነገር ነው።›› ብለዋል። ጥቂት የማይባሉት ደግሞ ፍቅረኛ ስለሌላቸው አክብረው እንደማያቁ፣ ነገር ግን ለወደፊት ቢያከብሩት ደስ እንደሚላቸው ተናግረዋል። የተወሰኑት ደግሞ በበዓሉ ባይስማሙም ሥራው የአንድ ቀን ብቻ ባለመሆኑ እንደሚሠሩት በፈገግታ ይገልጻሉ።

ነጋዴዎች ይህን ይበሉ እንጂ በዚህ ሐሳብ ዙሪያ ሰዎች የተለያየ ሐሳብ ሲሰጡ ይደመጣል። አዲስ ማለዳም የጥቂቶችን ሐሳብ ተካፍላለች።
ሳሙኤል ደበበ ከፍቅረኛው ጋር አራት ዓመታትን እንዳሳለፉ ይገልጻል። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ አንድም ቀን እንኳን ቫላንታይንን አክብረው እንደማያውቁና የማክበር ፍላጎትም እንደሌለው ያስረዳል። ‹‹ለእኔና ለፍቅረኛዬ ቀናቶች ሁሌም አዲሰ ቀን ናቸው። ምንም የተለየ ነገር የለም። ባህሉም ቢሆን እኔ የማልቀበለው ነገር ነው›› ሲል ያብራራል። ‹‹ይህ በዓል የፈጠረው ነገር ቢኖር ለሆቴሎች እና ለነጋዴዎች ቀኑን አስታከው ለሚሠሩ ጥሩ ከመሆን ውጪ፣ ሌላ ምንም የተለየ ነገር የለውም›› በማለት ያስረዳል።

‹‹ቀኑ የተለየ ነው። መከበሩ ምንም ችግር የለውም። ጥሩ የሆነውን ነገር ብንማር ምንም ችግር የለውም። እንደውም ከሌላ ጊዜ በተለየ ቀኑ የኛ ነው ብለን ማክበራችን ደስ የሚል የተለየ ትዝታ እንዲኖር የሚያደርገን ስለሆነ፣ ያለንን ፍቅር ስጦታ በመለዋወጥ ማሳለፍ የራሳችን ጊዜ ኖሮን ማሳለፍ ደስ የሚል ነገር ነው።›› ስትል የምታስረዳው ሳምራዊት ፍቅሩ የተባለች ወጣት ናት።

በግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ የምትሠራዋ ማሕሌት ገብሩ ደግሞ፣ ‹‹ፍቅረኛ አለኝ። ግን እለቱን እንደማንኛውም ቀን ነው የማየው።›› በማለት ጀመረች። እንዲህ ዓይነት ሐሳቦች ብዙም ደስተኛ እንደማያደርጓትም ነው የምታስረዳው።

አላዛር ዳንኤል የ28 ዓመት ወጣት ነው። ‹‹ፍቅረኛ የለኝም። የካቲት ስድስት የፍቅረኞች ቀን ተብሎ መከበሩ ለእኔ ምንም እንዲሰማኝ አያደርግም። ዛሬ ላይ ሆኜ ሳስበው ፍቅረኛ ኖራኝ የማከብር አይመስለኝም። ባህሉም ቢሆን የእኛ አይደለም። እኔ ላከብር ይቅርና የማውቀው ጓደኛዬ ለሌሎች ቀናቶች ፍቅረኛው ጋር ሲጣሉ እንደውም ሲደበድባት እመለከታለሁ። እለቱን ሲያከብሩ ሳይም ግርምት ይፈጥርብኛል። መከበሩም ለእኔ አሳማኝ አይደለም›› ባይ ነው።

ሆቴሎችስ?
በአዲሰ አበባ የሚገኙ ሆቴሎች የዘንድሮውን የፍቅረኞች ቀን በተመለከት ዝግጅት ማድረጋቸውን ለአዲሰ ማለዳ አስታውቀዋል።
ካፒታል ሆቴልና ስፓ ቀኑን ለፍቅረኞች ኹለት ዓይነት ፓኬጅ አዘጋጅቻለሁ ብሏል። ይህም ፍቅረኞቹ እራት ብቻ ተመግበው የሚዝናኑበት አማራጭ ያዘጋጀ ሲሆን፣ ለዚህም ዋጋው 1 ሺሕ 600 መቶ ብር ብቻ ነው ተብሏል። ሌላው ማደሪያን ጨምሮ ሲሆን ይህም እንደ ክፍሎቹ ዋጋ እንደሚወሰን ነው ሆቴሉ የጠቆመው።

የፍቅረኞችን ቀን ለማክበር ከተዘጋጁት ሆቴል መካከል ሌላው ራዲሰን ብሉ ሆቴል ነው። ሆቴሉ ለፍቅረኞች ኹለት ዓይነት ፓኬጆችን ማቅረቡን ለአዲሰ ማለዳ አስረድቷል። ያለ ገደብ ከአልኮል ነጻ የሆኑ መጠጦች፣ የአልኮል መጠጦችን ከብፌ እና ሙዚቃ በዲጄ ያዘጋጀ ሲሆን፣ ዋጋውም ተጨማሪ እሴት ታክስን ሳያካትት 1 ሺሕ 800 ብር እንደሆነ ነው የነገሩን።

የአበባ አምራቾች
ይህ ቀን ገበያቸው እንዲደራ ከሚያደርጋቸው ውስጥ የአበባ አምራቾች ይገኙበታል። በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃም የሚከብሩት ብዙ ሲሆኑ፣ በተለይም በአውሮፓ አገራት መከበሩ የአበባ ምርት ገበያው እንቅሰቃሴ እንዲጨምር ያደርጋል/አድርጓልም።

በደብረ ዘይት አካባቢ የሚገኘው ሰንራይዝ የአበባ አምራች ውስጥ የፋይናንስ ክፍል ኃላፊ አስናቀ ለአዲሰ ማላዳ ሲናገሩ፣ የአበባ ገበያው ከአምናው ጋር ምንም የተለየ ነገር የለውም። በእኛ በኩል የምርት አጥረት የለብንም። የአየር ንብረቱም ቢሆን አመቺ ነው ሲሉ በመግለፅ፣ ምርቶቻቸውን ለአገር ውስጥ ገበያ ሳይሆን አሜሪካ እና ጃፓንን ጨምሮ ወደ ሌሎች አገራት መላካቸውን ጠቁመዋል።

በፈረንጆቹ ከየካቲት 1 እስከ 13/2020 ባሉት ቀናት በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል 2 ሚሊዮን 66ሺህ 868 ኪሎ ግራም የአበባ ምርቶች ወደ ውጭ የተላከ ሲሆን ባለፈው ዓመት ደግሞ 1 ሚሊዮን 877 ሺህ 144 ኪሎ ግራም አበባ ተልኳል፡፡ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 189 ሺህ724 ልዩነት እንዳለው የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማህበር የማስታወቂያ እና መረጃ አገልግሎት ኃላፊ የምሥራች ብርሃኑ ለአዲሰ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

ቄስ ቫላንታይን ሲታወሱ
ዘመኑ 270 ላይ ነበር። በዚህ ጊዜ የሮማው ንጉሥ የነበረው ንጉሥ ካላውዲዮስ አንድ አዋጅ አወጀ። አዋጁም በሮም የሚኖሩ ማንኛውም ወንዶች ትዳር እንዳይዙ ይልቁንም በውትድርና እንዲያገለግሉ በሚል የተላለፈ ነበር። በዘመኑም ‹‹ይህማ እንዴት ይሆናል!›› ያሉት የሮማው ቄስ ቫላንታይን፤ የንጉሡን አዋጅ ወደ ጎን በመተው የሮም ወጣቶችን በምስጢር ወይም በድብቅ ማጋባት ጀመሩ።

ድርጊታቸው ያበሳጫቸው ንጉሥ ካላውዲዮስ፣ ቄስ ቫላንታይንን የማያደግም እርምጃ እና ለሌሎችም ማስተማሪያ ያሉትን አደረጉ። ቄሱንም በስቅላት እንዲሞቱ አደረጉ። ቄስ ቫላንታይን በየካቲት ወር በሰባተኛው ቀን ለፍቅር ሲሉ ሕይወታቸው በማጣታቸው የማስታወሻ በዓል እንደሆነላቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
አሁንም ግን ‹በዓሉ መከበሩ ለኢትዮጵያ ምኗ ነው?› ሲሉ የሚጠይቁ ብዙዎች ናቸው። ነገሩ ዛሬም ድረስ በአከራካሪነቱ እንደቀጠል ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 67 የካቲት 7 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here