ከየት እንጀምር?

0
743

ባለፈው ሳምንት የወለደች እህታችንን ለመጠየቅ ወደ የካቲት ሆስፒታል አቅንተን ነበር። በዛን ቀን የተወለዱትን ያህል ልጆች በየአንዳንዱ ሆስፒታልና በየአንዳንዱ ቀን የሚወለዱ ከሆነ፣ የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር ከታሰበው ጊዜ ፈጥኖ ራሱን እጥፍ ሊያደርግ እንደሚችል ጠረጠርኩ። ጥርጣሬዬ ወደ ጎን ይቀመጥና፣ ትዝብቴን ላኑር።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ በዓለም አገራት ፊት ደሃ ለመባል ልታሟላ የሚገባውን መስፈርት ሁሉ በብቃት አሟልታለች። ለዚህ ማሳያ ሊሆኑ ከሚችሉ ተቋማት መካከል ደግሞ የሕክምና ማእከሎች ተጠቃሽ ናቸው። ያልተሟላ መሠረተ ልማታቸው ለአንድ ታካሚ ከሕመሙ ላይ የሚደመሩ አስጨናቂ መከራዎች ሆነው ይታዩኛል።

እንዳልኳችሁ የካቲት ሆስፒታል በገባሁ ጊዜ ይህን ምስኪን የሆነ ገጻችንን ነው ያየሁት። የማዋለጃ ክፍሉን የማየት እድል ባይገጥመኝም፣ የወለዱ ሴቶች በተለይም በቀዶ ጥገና ልጅ የተገላገሉ እናቶች የሚያርፉበትን ክፍል አይቻለሁ። ያሳዝናል። ይህንንም በኹለት መንገድ እዩልኝ።

አንደኛ በእጃችን ባለ ነገር ማድረግ ያልቻልነው ነው መጀመሪያ የታየኝ። ይህም ከክፍሉ ንጽህና ይጀምራል። ስለ ሕጻናት ደኅንነት፣ ስለ እናቶች ጤናማነት ካነሳን አንድም ከዚህ ይጀምራል፤ የሚወለዱበትና የሚወልዱበት ነውና ክፍላቸውን በጥንቃቄ ከመያዝ።

ሌላው መደረግ እያለበት ያልተደረገው ነው። ለምሳሌ የአልጋዎቹ ሁኔታ፣ ጠያቂ ያለጥንቃቄ እንዲገባ መፈቀዱ፣ በአዳራሹ አካባቢ ያለ የመጸዳጃ ቤት ሽታ፣ መጸዳጃው ለወላድ ምቹ አለመሆኑ ወዘተ ሊነሳ ይችላል። ይህን ማስቀረት ሲገባ አልተደረገም። ብቻ ምን አለፋችሁ ምንም ደስ አይልም፤ ከፍ ሲል ያስቀይማል።

ያ ብቻ ሳይሆን ጠጋ ብሎ የወለዱ ሴቶችን ላናገረ ቅሬታቸውን ይሰማል። ያንንም ጠይቄ ሰምቻለሁ።በተለይም ባለሞያዎች እንደሚሳደቡ፣ እንደሚያመናጭቁና የሴቶቹን ሕመም አብዝተው ከማየትና ከመልመዳቸው የተነሳ፣ ሕመማቸውን ንቀው ቁጣ እንደሚቀድማቸው የወለዱት ሴቶች ይናገራሉ። ‹አትቅበጪ!› የሚሉም አይጠፉ።

ይህን ስል ሁሉንም የማዋለጃ ክፍል ላይ የሚሠሩ ባለሞያዎች ስወቅስ፣ እንዲሁም የካቲት ሆስፒታልን ሳነሳ ሆስፒታሉን በተለየ ለመኮነን አይደለም። እንደውም ‹ይሄ ነገር ድሮም ነበር ወይ?› ብዬ የጠየኳቸውና በተለያዩ የመንግሥት ሆስፒታሎች የወለዱ ሴቶች እንደነገሩኝ፤ ‹እድለኛ ከሆንሽ ጥሩ አዋላጅ ሐኪምና ነርሶች ይደርሱሻል፤ የእድል ጉዳይ ነው› ብለውኛል።

እርግጥ ነው፤ ይሄ የድህነታችን ውጤት ነው። ለሆስፒታሉ በጀት ይጨመር፣ መንግሥት ትኩረት ይስጠው፣ ክትትል ይደረግበት፣ ባለሞያዎች ሙያቸውን ያክብሩ ወዘተ እያልኩ አላሰለቻችሁም። አሁን እንደገባኝ ከሆነ ‹እገሌ ይህን ያድርግ› ብሎ ሐሳብ መስጠት የሚያዋጣ አይደለም። ‹እኔ ምን ላድርግ?› ብሎ ራስን መፈተሸና መጠየቅ ነው የሚያስፈልገው።

በተዘዋዋሪ ሐሳብ መስጠቴ ግን አይቀርም። አዎን! በዚህ ላይ በሴቶች መብት ዙሪያ የሚሠሩ ተቋማት በቀላሉ ትልቅ ተጽእኖ መፍጠር እንደሚችሉ አምናለሁ። አንደኛው የመውለጃ ክፍሎችን በቀላሉ ውብና ማራኪ እንዲሁም ንጹሕ ማድረግ ነው። ይህም ባለሞያዎቹን ሊያግዝ ይችላል። አዋላጅ ባለሞያዎችም የሁሉን ሴቶች ሕመም በትዕግስት እንዲያስተናግዱ መጠየቅ ይገባል። ለእናቶች ክብር ይገባልና፤ መውለድ ቀላል ሥራ አይደለምና።

በገጠር በወሊድ ምክንያት አንዲትም እናት መሞት የለባትም እያልን፣ በከተማ ለዐይን በሚጨንቅና በሚያስቀይም አዳራሽ ውስጥ የወለዱ ሴቶችን ማየት ያሳዝናል። እንዳልኩት ነው፤ ይህ ይስተካከል ብለን ወደ ማንም ልንጮኽ አንችልም። በሴቶች ጉዳይ ላይ ለሚሠሩ ተቋማት ግን ይህን ጥሪዬን አስተላልፋለሁ። በትንሹና በቀላል ወጪ ልናደርግ የምንችለውን ለእነዚህ ወላዶች እናድርግ።

ሕጻናትን በመልካም ስፍራ እንቀበላቸው። ወግ ይድረሰንና የእናቶችን ሞት ማስቀረት ቅንጦት ሳይሆንብን፣ እንደውም ለእናቶችም ክብር በሚሰጥ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጡ የሐኪም ቤቶቻችንን አዳራሾች እንቃኛቸው።
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 67 የካቲት 7 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here