በምሥረታ ላይ ከሚገኙት የእስላሚክ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው ሂጅራ ባንክ የአክሲዎን ሽያጭ መጨረሱን ተከትሎ፣ በ700 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ወደ ሥራ ለመግባት የብሔራዊ ባንክን የፍቃድ ማረጋገጫ እየጠበቀ መሆኑ ታወቀ።
የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር መከሚል በትሩ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ ሂጂራ ባንክ ቅድመ ሥራዎችን አጠናቆ የመስራቾች ጉባኤውን አካሂዶ ፈቃድ ለማግኘት የሚያስፈልጉ መረጃዎችን አሟልቶ ለብሔራዊ ባንክ ያስገባ ሲሆን፣ የፍቃድ ማረጋገጫ እየጠበቁ እንደሆነ ተናግረዋል።
ባንኩ ወደ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የተከፈለ ካፒታል የሰበሰበ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 700 ሚሊዮን ብር የሚሆነው የተከፈለ መሆኑ ተረጋግጧል።
መከሚል እንደገለፁት ባንኩ ብሔራዊ ባንክ ፍቃድ ከሰጠው፣ በፍጥነት 20 ቅርንጫፎችን ይከፍታል። በዓመት ውስጥም ቁጥሩን ወደ 40 ያደርሳል ብለዋል። ባንኩ 9 ሺሕ ባለድርሻዎች ያሉት ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 200 ያክሉ ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራዎች ናቸው። “የባንኩ የገንዘብ መርህ ወደታች ወርዶ ሰፊዉን ኅብረተሰቡን ይዞ መነሳት ነው። እንደ ቢዝነስ ሞደል ይዞ የተነሳዉ ሰፊዉን አነስተኛ ገቢ ያለውን ማኅብረሰብ ለመጥቀም እንጂ ጥቂት ባለሀብቶችን አቅፎ መንቀሳቀስ አይደለም” ሲሉ መከሚል ገልፀዋል።
“ሂጂራ ባንኩ ውስጥ አንድም ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰብ የለም” ያሉት መከሚል፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚባለዉ በብሔራዊ ባንክ ሕግ መሰረት በባንኩ ላይ ከኹለት እስከ አምስት በመቶ የሚሆን ድረሻ ያላቸዉ ግለሰቦች ሲኖሩ እንደሆነ አብራርተዋል።
ባንኩ የሚሰጣቸዉ አገልግሎቶች በዋናነት በሦስት ዘርፎች እንደሚሆን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ሂጂራ ባንክ ወደ ሥራ እንደገባ የሚሰጣቸዉ አገልግሎቶች ንግድን ከማቀላጠፍ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች፣ ኢንቨስትመንት፣ ከወለድ ነፃ ብድር ሲሆን፣ በዋነኛነት ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን አገልግሎታቸውን ንግድን ከማቀላጠፍ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው አገልግሎቶች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ መከሚል ጠቁመዋል።
ባለፉት ዐስርት ዓመታት ውስጥ ምንም ዓይነት ባንክ የፋይናንስ ኢንዱስትሪውን ያልተቀላቀለ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲያ፣ 12 ሙሉ እስልምና፣ የኮንስትራክሽን እና የቤት፣ ኢንቨስትመንት፣ ብድር እና መደበኛ ባንኮች እየተቋቋሙ ናቸው።
ቅጽ 2 ቁጥር 68 የካቲት 14 2012




ብድር በጊዜ ቢገኝ ጥሩ ነበራ።ለምሰሌ እኔ ህንመሣሪያ ነገዴ ነኝ ሥራዬን አቀላጥፌ ለመስራት የገንዘብ እጥረት አለብኝ ።ስለዝ ባንኩንም ለመጥቀም ራሴም ለመጠቀም ዝጉጁ ነኝ ።ምላሽ እጠብቀለሁኝ።