በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሱዳን ሊሻገሩ የነበሩ 96 ሴቶች ተያዙ
በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሱዳን ለመሻገር የሞከሩ 96 ሴቶች መያዛቸውን የጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ ገለጸ። ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡት ሴቶች፣ ጎንደር ከተማ ባረፉበት ሆቴል ውስጥ ከህብረተሰቡ በተሰጠ ጥቆማ መያዛቸውን የጎንደር ከተማ ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የስልጠናና ግንዛቤ ማስጨበጥ ንዑስ ክፍል ኃላፊ ዋና ሳጅን ታደሰ አለምነህ ተናግረዋል። አሁን ላይም ሁሉም ሴቶች በፖሊስ ጣቢያው የሚገኙ ሲሆን፣ በህገ ወጥ ደላሎች በአዲስ አበባ በኩል የሚደረጉ ጉዞዎች ተከልክለዋል በሚል የስደት ተጓዞቹን ወደ ጎንደር በምሽት በመላክ ከ15 እስከ 20 ሺህ ብር እንዳስከፈሏቸውም ጠቅሰዋል። (ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት)
…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………
ኢትዮ ቴሌኮም ለወራት ሲያካሂድ የቆየውን የማስፋፊያ ስራ በማጠናቀቅ በቪፒኤን አገልግሎት ላይ የ 72 በመቶ ቅናሽን ጨምሮ የፍጥነት እና የዋጋ ማሻሻያዎችን ማድረጉን አስታወቀ። ቴሌኮሙ ዛሬ በሽራተን አዲስ እያካሄደ ባለው ጉባኤ ላይ ይፋ እንዳደረገው ከ 12 ሚሊዮን ዶላር ባላይ ወጪ ያደረገበትን ይህንን ማስፋፊያ ከመጪው ሰኞ የካቲት 23 በኋላ ስራ ያስጀምራል። ለብሮድባንድ ኢንተርኔት ተጠቃሚ ድርጅቶች የ 65 በመቶ የዋጋ ቅናሽ ያካሄደው ቴሌኮሙ አራት እጥፍ ፍጥነት ያለተጨማሪ ዋጋ ማድረጉንም አስታውቋል። እንደ ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ፍሬህይወት ታምሩ ገለፃ የብሮድ ባንድ ኢንተርኔት ለመኖሪያ ቤት ለሚጠቀሙ ደንበኞቹ የ 69 በመቶ የዋጋ ቅናሽ እና ሶስት እጥፍ ፍጥነት መጨመሩን ገልፀዋል። አገልግሎቱም በመላው አገሪቱ ተደራሽ ይሆና ተብሏል። (አዲስ ማለዳ)
…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ኤርሚያስ አመልጋ ከአስር አንዲፈቱ ለፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ደብዳቤ መጸፋን ጠበቃቸው መናገራቸው ተገለጸ። ኤርሚያስ አመላጋ ከእስር እዲፈቱ 21 ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ መጠየቃቸው የተነገረ ቢሆንም በኋላ ላይ ግን ጠበቃቸው ከማረሚያ ቤቱ የጸጥታ ቡድን ጋር በመጋገር ጉዳዩን መፍታት እንደቻሉ ተነግሯል። (አዲስ ስታንዳርድ)
…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………
በአዲሱ ማሻሻያ መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ ከባድ ተሽከርካሪዎች ጠዋት ከአንድ ሰዓት እስከ ሦስት ሰዓት እንዲሁም ከሰዓት ከ10:30 እስከ 12:00 ሰዓት ውጪ ባሉ ሰዓታት እንዲንቀሳቀሱ ተወስኗል። ማሻሻያው የተደረገው የተለያዩ ተቋማት በሰዓት ገደቡ ምክንያት በተለይም የግንባታ ሥራዎቻቸውን ለማከናወን መቸገራቸውን ገልጸው ቅሬታ በማቅረባቸው እንደሆ የከንቲባ ጽኅፈት ቤት አስታውቋል። (የከንቲባ ጽኅፈት ቤት)
…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድር ወስደው ያልመለሱ እና የጠፉ 71 ባለሃብቶች እና ሰራተኞቹን በሕግ ለመጠየቅ እንዲሁም ያለአግባብ የባከነ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ግንዘብን ለማስመለስ ምርመራ ማድረግ መጀመሩን አስታወቀ።ምርመራው ሲጠናቀቅ አስተዳደራዊ እና ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ የባንኩ ፕሬዝዳንት ኃይለየሱስ በቀለ ዛሬ ጠዋት በጽህፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቀዋል። ከዚህ በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት ከዚኅ ቀደም ከባንኩ ብድር የወሰዱ 38 ፕሮጅክቶች መውደማቸውንም ኃይለየሱስ ተናግረዋል። ምርመራ እየተደረገባቸው ያሉትን ድርጅቶች እና ባላሃበቶች ስም ዝርዝር ከመናገር ግን ተቆጥበዋል። (አዲሰ ማለዳ )
…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………
በቢሾፍቱ የሚገኘው የኢፌዴሪ አየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ በዛሬው ዕለት የካቲት 19/2012፣ 106 ለሚሆኑ ከፍተኛ መኮንኖች ሹመት ሰጠ። ሹመቱን የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄነራል ይልማ መርዳሳ ሰጥተዋል።
የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላም በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን የአገር የመከላከያ ሰራዊትን ለማፍረስ የሚጥሩ በርካታ አካላት እንዳሉ ጠቁመዋል። ከሹመቱ በተጨማሪ ላለፉት 6 ወራት በስልጠና ላይ የቆዩ የአየር ኃይል ወታደራዊ ፖሊስ አባላት ምረቃ ተከናውኗል።(ኢቢሲ)
…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………
ህንፃ ተከራይተው ለሚገኙ 77 የፌደራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች ኪራይ በዓመት 1 ቢሊዮን ብር እየተከፈለ መሆኑ ተገለጸ። በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ስር የተደራጀው ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ተክለፃዲቅ ተክለአረጋይ እስካሁን 30 ለሚሆኑ መስሪያ ቤቶች ቢሮ መገንባቱን ጠቁመዋል። በዚህም በየወሩ መንግሥት በትንሹ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ማዳን መቻሉን ገልጸዋል። (አሐዱ ቴሌቪዥን)
…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………………
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ባለፉት ሰባት ወራት 24 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ገለጸ።
ባለፉት ሰባት ወራት 25 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 24 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ገልጿል። የተሰበሰበው የግብር ገቢ የዕቅዱን 95 በመቶ መሆኑንም ቢሮው አስታውቋል። ገቢው ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ14 በመቶ ዕድገት ማሳየቱ ተመላክቷል። (ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት)



