የካቲት 17/2012 የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሦስት ጽሕፈት ቤቶችን በተመለከተ ለፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የጻፈው የትብብር ደብዳቤ፣ ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ጋር በቀጥታ የሚያያዝ አይደለም ሲል ፓርቲው ለአዲስ ማለዳ ገለፀ።
ከኢዴፓ ጋር ምንም ዓይነት ንትክር ውስጥ መግባት አንፍልግም ያሉት የኢዜማ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናትናኤል ፈለቀ፣ ኢዜማ ሲመሠረት የተለያዩ ፓርቲ አባላት የነበሩ ሰዎች ፓርቲያቸውን አክስመው ኢዜማን እንደ ግለሰብ ነበር የተቀላቀሉት ሲሉም አስረድተዋል።
ይህንን መሠረት በማድረግ አዲስ ለሚመሠረተው ፓርቲ ጥቅም ላይ ይዋል ብለው የወሰኗቸው ውሳኔዎች ነበሩ፣ በዛም ውሳኔ መሰረት ኢዜማ የሚጠቀማቸው ንብረቶች መኖራቸውን ናትናኤል ጠቁመዋል።
ምርጫ ቦርድ የወሰነው ውሳኔም ቢሆን ከኢዜማ ጋር በቀጥታ የማይያዝ መሆኑን በመግለጽ፣ የሚያያዘውም ከኢዴፓ ጋር መሆኑንን ተናግረዋል።
ኢዜማ ከኢዴፓ ጋር የሚያገኛኘው ምንም ነገር የለም በማለት የሚናገሩት ናትናኤል፣ ኢዜማ ውስጥ የገባው ኢዴፓም ሆነ ምርጫ ቦርድ ከኢዜማ ጋር ተያይዞ የሚያቀርቡት ጥያቄ፣ የሚመለከተው ውሳኔውን ከወሰኑት ግለሰቦች ጋር እንጂ ከኢዜማ ጋር አይሆንም ብለዋል።
ናትናኤል አክለው እንዳሉት፣ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ እስከ አሁን እኛ ጋር የመጣልን ጥያቄ የለም በማለት ተናግረዋል። ጥያቄው ሲመጣም ተገቢውን ምላሽ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።
ይልቁንም ‹‹አሁን ላይ ኢዜማ ያሉት ሦስት ጽሕፈት ቤቶቹ የተለያየ ቦታ በመሆናቸው እንዲሁም አሁን ባለንበት ሁኔታ ጽሕፈት ቤቶቹ ለሥራ አመቺ ባለመሆናቸው ብሎም ቢሮዎቹም ስለጠበቡ በእኛ በኩል ለፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጽሕፈት ቤት እንዲሰጠን ጠይቀናል። ይህ ከሆነም ጽሕፈት ቤቶቹን ለቤቶች ኮርፖሬሽን የምንመልስ ይሆናል›› ብለዋል ናትናኤል።
ኢዜማ እስከ አሁን ድረስ ጽሕፈት ቤቶችን በተጨባጭ አለማግኘቱን ለአዲሰ ማለዳ አስታውቋል። በኢዴፓ በኩልም የክስ ወረቀት እንደደረሳቸው ናትናኤል ጠቅሰዋል።
ኢዴፓ በበኩሉ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የጻፈለትን የትብብር ደብዳቤ መሰረት በማድረግ ሦስት ጽሕፈት ቤቶቹ እንዲመለሱለት የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽንን እንደሚጠይቅ ለአዲሰ ማለዳ ገልጿል።
በኢዴፓ እና በኢዜማ በኩል የነበረውን አለመግባባት ምርጫ ቦርድ አስቀድሞ መፍታት ሲኖርበት ዘግይቶም ቢሆን ተገቢ እርምጃ መውሰዱንም የኢዴፓ ፕሬዝዳንት አዳነ ታደሰ የገለጹ ሲሆን፣ ቀጣዩ ሥራችን የሚሆነው የቤቶች ኮርፖሬሽን አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወስድ መጠየቅ ነው ብለዋል።
ኢዴፓ በኢዜማ ላይ መሥርቶት የነበረውን ክስ ጽሕፈት ቤቶቹ መመለሳቸውን እርግጠኛ ሲሆን፣ ክሱን ሊያቋርጠው እንደሚችል አዳነ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፣ በኹለቱ ፓርቲዎች መካከል የነበረውን አለመግባባት ለምፍታት ዘግይቶም ቢሆን እርምጃ ወስዷል መባሉን ሳይቀበለው መቅረቱን ለአዲስ ማላዳ አስታውቋል። የቦርዱ ሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ፣ ቦርዱ አለመዘግየቱን በመግለጽ እንደውም የሠራው ሥራ የትብብር እንጂ ይህን የማድረግ ግዴታ የሌለበት መሆኑን አስረድተዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012



