ዐስር የአማራ እና የኦሮሚያ ፓርቲዎች ውይይት ጀመሩ

0
437

ከኹለት ሳምንት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ዐስር የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ፓርቲዎች በተገኙበት፣ በኹለቱ ክልል ሕዝበች ጥያቄዎች እና በልሂቃኖቻቸው መካከል መቀራረብ መፍጠርን መሠረቱ ያደረገ ውይይት ተካሂዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል ግጭቶች በተነሱ ወቅት ያሰባሰቧቸው እነዚህ ፓርቲዎች፣ ለኹለተኛ ጊዜ ተገናኝተው ተወያይተዋል። በውይይቱ ላይ የኦፌኮ አባል መሆናቸውን ይፋ ያደረጉት ጃዋር መሐመድ፣ የጥናት ወረቀት ያቀረቡ ሲሆን በዛ መነሻም ውይይቶች ተካሂደዋል።

የኦሮሞ እና የአማራ ጥያቄዎች ምንድን ናቸው የሚሉ ሐሳቦች የተነሱ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ጉዳይም አንዱ የውይይታቸው አጀንዳ እንደነበር አዲስ ማለዳ ከታማኝ ምንጮቿ ሰምታለች።

ሌንጮ ለታ፣ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) እና አንዳርጌ (ዶ/ር) ውይይቱን የመሩ ሲሆን፣ የአማራ እና የኦሮሞ ምሁራን መማክርቶች ውይይት እንዲካሄድ ካነሳሱ መካከል ናቸው።

ይህ ለመገናኛ ብዙኀን ዝግ የነበረው ውይይት አወያይ የነበሩት ዲማ፣ በኹለቱ ሕዝቦች መካከል ሰላም እና ችግርም ካለ በውይይት ሊፈታ የሚችልበትን ሁኔታ ለማመቻቻት ያሰበ ውይይት መሆኑን ገልፀዋል። የፖለቲካ ውድድርን ሰላማዊ ማድረግም ዋነኛ ዓላማው እንደሆነም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

‹‹ይሄ መድረክ በኹለቱ ክልል ፓርቲዎች ላይ ተገድቦ የሚቀር ሳይሆን አገር አቀፍ መሆን አለበት። ከዚህ በላይ ማደግ ይገባዋል›› ብለዋል። ‹‹ይህም ለብሔራዊ ውይይት መንገድ የሚያመቻች እና ወደዛው የሚሄድ ነው›› ያሉት ዲማ ‹‹በተመሳሳይም በሌሎች አካላት መካከል መሰል ውይይቶች አሉ። ያንን ተከትሎ ቀጣይ ውይይቶች ይኖራሉ›› ብለዋል።

ከአማራ ክልል ፓርቲዎች ከሚወያዩት ፓርቲዎች መካከል የሆነው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀ መንበር በለጠ ሞላ፣ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ውይይቱ ከአማራ ክልል ውጪ የሚኖሩ የአማራ ክልል ነዋሪዎችን መብቶች ለማስጠበቅ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

‹‹እንዲህ አይነት ውይይቶች እና ክርክሮች አስፈላጊ ናቸው። በተለይ በእነዚህ ትልልቅ ሕዝቦች መካከል በጣም አስፈላጊ ነው›› ሲሉም ገልጸዋል። ‹‹እነዚህ ሕዝቦች ትልልቅ ናቸው ማለት ማንንም ሊያስከፋ አይገባም። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኹለቱ ሕዝቦች ልሂቃን ውይይት፣ ንግግርም ቢሆን ፉክክር የኢትዮጵያን ነገ ይወስናል። በሁሉም ነገር ባንግባባም የምንግባባውን ያህል መሄድ ግን እንችላለን›› ብለዋል።

የሐሳብ ፍትጊያዎች ይኖራሉ ያሉት በለጠ፣ ይህን ግን ፓርቲያቸው እንደማይጠላውና እነዚህ ፍጭቶች በሐሳብ ላይ ስለሆኑ ጠቃሚ ናቸው ብለዋል። ኹለቱ አካላት በአንድ ጣራ ስር ሆነው መወያየት መጀመራቸው በራሱ ሊያስደስተን ይገባል ብለዋል። በለጠ አክለውም ‹‹ከዚህ ውጪ ሌላ አማራጭ የለም። ሌላ አማራጭ አለ ካልን ለማንም አይበጅም›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

‹‹በልዩነት ተስማማቶ ነገር ግን የሚያስማሙንን ፈልጎ ማግኘት፣ ይሄ ከኹለቱም አካል የተወከሉ ፓርቲዎች ላይ የተጣለ ኃላፊነት ሲሆን፣ ይህንንም ኹለታችንም ወደነው ነው እያደረግነው ያለንው›› ብለዋል። ‹‹ይሄ ሲዳብር ለኢትዮጵያ የሚበጅ እውነታን ይወልዳል›› ሲሉም ተናግረዋል።
ውይይቱ ላይ ኦነግ፣ አብን፣ ብልፅግና (ከኦሮሚያ እና ከአማራ) ከተሳታፊ ፓርቲዎቸ መካከል ናቸው።

ቅጽ 2 ቁጥር 69 የካቲት 21 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here