አርብ መጋቢት 25/2012 ጠዋት በፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የቀረበው ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ላይ ቀሪ ምርመራዎችን ለማካሄድ ፖሊስ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቁን ተከትሎ የስድስት ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተፈቀደለት።
የጋዜጠኛውን መታሰር የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅቱ (ሲ.ፒ.ጄ.) ያወገዘ ሲሆን፣ ጋዜጠኛው በአፋጣኝ እንዲፈታ ሲልም መጠየቁን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል።
ጋዜጠኛው የታሰረው መጋቢት 17/2012 ሲሆን፣ የታሰረበት ምክንያትም ‹ኢትዮ ፎረም› በተሰኘ የዩ-ትዩብ ቻናል ያሰራጨው መረጃ እንደሆነ ተገልጿል። መረጃውም ‹መንግሥት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት 200 ሺሕ ጉድጓዶች እንዲዘጋጁ አዝዟል›› የሚል ነበር።
በማግስቱ በቅርብ ዘመዳቸው መኖሪያ ቤት በቁጥጥር ስር የዋሉት ያየሰው፣ ፖሊስ በወንጀል ሕጉ ላይ ‹ሐሰተኛ መረጃ በማሰራጨት የተደነገገውን ተላልፈዋል› ሲል እንደጠረጠረው ተጠቅሷል። ያየሰው በጉዳዩ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረበው ቅዳሜ መጋቢት 19/2012 ሲሆን፣ ለፖሊስ የስድስት ቀን የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ ተፈቅዶ እንደነበር ይታወሳል።
ጋዜጠኛ ያየሰው ‹ኢትዮ ፎረም› የተሰኘ በትግራይ ቴሌቪዥን ጣቢያ የሚተላለፍ ሳምንታዊ የቴሌቪዥን የቃለመጠየቅ መሰናዶ አዘጋጅ ነው።
ቅጽ 2 ቁጥር 74 መጋቢት 26 2012


