የኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወራትን ተሻግሮ ተጨማሪ የሚቆይበትን ወራት መገመት በማይቻልበት ሁኔታ አሁንም ሐሳቡን ሳይቀይር እየተሰራጨ ይገኛል። ዓለምም ይህን ለመቋቋም በአንድ ጎን ሳይንሱን በሌላ በከል እምነትን በሃይማኖት በኩል ተስፋ አድርጋ እየጠበቀች ነው። የሕክምና ባለሞያዎች ከእረፍት ተለይተው ይሯሯጣሉ። መንግሥታት የሚያደርጉት ቸግሯቸው በየእለቱ አዳዲስ መመሪያና ሕግ ያወጣሉ። ሌላውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ ጉዳይ ለማሰብ ጊዜ የለም፣ ሁኔታም አይፈቅድም።
የፋሲካ በዓል በዚህ የኮሮና ሰሞን መሆኑ ለምዕመናኑ ቀላል አልሆነም። የገበያ ግርግርና የንግድ ተቋማት መጨናነቅ ቀንሷል። ሆኖም ግን እንደ ቫይረሱ የስርጭትና የመተላለፍ ባህሪ፣ ወደ መቶ የሚጠጋ ሰው በቫይሱ እንደተያዘባት አገርም የሆንን አይመስልም፤ ‹‹አንድ ሺሕ እስኪገባ ድረስ እንደ ልብ ለመሆንና ላለመፍራት እድል አለን› የተባለ ነው የሚመስለው።
አሁን በዓሉ እንዲህ በቀንና በሰዓታት ልዩነት በቀረበ ጊዜ ደግሞ፣ የዶሮና የበግ ገበያው ከወዲሁ አስጨንቋል። በማኅበራዊ ሚድያው ‹‹ምን አለኝ ሽሮ…በቂቤ›› ያሉ አልጠፉም፤ የበግና የዶሮ ግብይት ለቫይረሱ ስርጭት ጥሩ አጋጣሚ ይሆናል የሚል ስጋት ገብቷቸዋልና ነው። ‹‹አንድ ቀን ሥጋ ባይበላ አይሞትም!›› ያሉም አልጠፉ።
እንዲያም ሆኖ ሰዉ ዶሮም ሆነ በግ ከመግዛት የሚቆጠብ ያልመሰላቸው ደግሞ በአንጻሩ፣ ‹‹በግና ዶሮ ሲገዙም ሆነ ሲሸጡ ጥንቃቄ ይደረግ›› ብለዋል። ይህም ታድያ ለእርድ የተገዛ በግን ማጠብንም ይመለከታል። ጾሙን በሥጋ ካልፈታሁ፣ በግ ካላረድኩ፣ ልጆቼ በግ ካልታረደ ደስ አይላቸውም፣ በግ ታርዶ ደሙ ካፈሰሰ በዓሉ በዓልም አይመስለኝ…የሚል ካለ፣ እንግዲህ በግ ለማጠብ ትዕግስት ያስፈልገዋል፤ ለጤናው ካሰበ።
‹‹በግ ማጠብ ለዱለት ጨጓራ እንደማጠብ አይደለም። ሽታውም ከባድ ነው። እንደው ቢቀርብንና ቤት ባፈራው ጾም ፈትተን ይህ ቀን ሲያልፍ ብናርድስ፣ የት ይሄድብናል?›› አንድ የማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚ የገበያ ፎቶ ጋር አያይዛ ያኖረችው ጽሑፍ ነው።
አንዱ ደግሞ በግ ሲገዛ ያለውን ሂደት እንዲህ ያብራራል፤ ‹‹የእኛ ልማድ እንዲህ ነው። በግም ሆነ ፍየል ስንገዛ ጀርባውን ጨበጥ ጨበጥ አድርገን ነው። ላቱ፣ ማጅራቱ፣ እግሩጥርሱ እያሉ ያገላብጡታል። ዶሮም ቢሆን ከመጨመቅ አይድንም። እና ስንት ሰው እንዲህ እንደሚነካ አስቡት! አንድ ቫይረሱ ያለበት ሰው የነካውን በግ ሌላው ከነካውም በሽታውን ስንት ሰይ ይዞ ቤቱ እንደሚሄድ አስባችኋል?››
እናም በዚህ ሐሳብ ስር የተሰጡ አስተያየቶች ውስጥ የገዙትን በግ ማጠብ መፍትሔ ነው የተባለ ቢሆንም፣ ታግሶና ሽታውን ተቋቁሞ በጉ ቢታጠብ እንኳ፣ ጸድቶ የሚጸዳ አይሆንም የሚል ነጥብ ተነስቷል። ከሁሉ ከሁሉ ግን ‹ቢቀርስ!› ያለው ብዙ ነው።
በሌላ በኩል እንኳን ወደ ሆድ የሚገባ ሥጋ እና የሥጋ ዘመድስ እንዳይገናኝና ይህ ቀን እስኪያልፍ እንዲራራቅ ተብሎ የለ ወይ ያሉም አሉ። ‹ሰው መቼም ከሆድ ይበልጣል› በማለት ነው። በተጓዳኝ ደግሞ ‹ቤታችሁ አልመጣም! ቤቴ አትምጡ። በስልክ እንጠያየቅ› የሚል መልዕክት ተላልፏል። በተለይም ሰው ቤት እንደማይሄዱ እርግጠኛ የሆኑ ነገር ግን ሰው ቤታቸው እንደማይመጣ እርግጠኛ ያልሆኑ፣ ከወዲሁ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 76 ሚያዝያ 10 2012


