የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ 10 በመቶ ጭማሪ አሳየ

0
925

ኢትዮጵያ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ወደ ውጭ ከላከቻቸው ምርቶች የተገኘው ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ10 በመቶ እድገት ማሳየቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በ2012 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት አጠቃላይ ከውጭ ንግድ የተገኘው ገቢ 2.09 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያቤቱ አስታውቋል። ይህም የተመዘገበው ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ከነበረው 2.68 ቢሊዮን ዶላር 78 በመቶ እንደሆነ ተጠቁሟል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በወቅታዊ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት እየተቀዛቀዘ ከመጣው የምጣኔ ሃብት ማሽቆልቆል ጋር ሲነጻጸር የአገሪቱ የውጭ ንግድ ገቢ ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ መሆኑን እና እስካሁን ያጋጠመ ችግር አለመኖሩን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መላኩ አለበል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ እንደተናገሩት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በሰው ልጆች ጤንነት ላይ ከሚያስከትለው አደጋ ባልተናነሰ በዓለም የምጣኔ ሃብት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። በዚሁም ሳቢያ በአሁኑ ወቅት በዓለማችን በርካታ አገራት ላይ የምርት እንቅስቃሴ እንዲገታ፣ ኢንዱስትሪዎች ምርት እንዲያቆሙ፣ የፋይናንስ ተቋማት እክል እንዲገጥማቸው እና አልፎ አልፎም ህገወጥ ድርጊት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

ይህ በሆነበት ሁኔታ የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ገቢ በተፈጠረው ድንገታዊ ችግር እስካሁን ያልተጎዳበትና እና በነበረበት አፈጻጸም የቀጠለው ኢትዮጵያ በብዛት ወደ ውጭ አገራት የምትልካቸው ምርቶች ምግብ ነክ በመሆናቸው እስካሁን መቀዛቀዝ እንዳልታየ ሚኒሰቴሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ሚኒሰቴር አክለውም እንደ ቡና ያሉ ምርቶች ተፈላጊነታቸው ከወቅቱ ጋር በተፈጠረ እድል እየጨመረ መምጣቱን አመላክተዋል።

በሌላ በኩል አሁንም ከወቅቱ ሁኔታ ጋር በተገናኘ በኢትዮጵያ ተመርተው ወደ ሌሎች አገሮች የሚላኩ የአበባ፣ ጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ላይ የተቀባይ አገራት ፍላጎት መቀዛቀዝ እንደታየ ሚኒስቴሩ ተናግረዋል። ሚኒስቴሩ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከወቅቱ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በውጭው ገበያ ተፈላጊነታወቹ የቀነሱ የአገር ውስጥ ምርቶች የምርት ስራቸውን ወቅቱ በሚፈልገዉ መልኩ እንዲያሽጋግሩ እና የሚያመርቱትን ምርት ተፈላጊ በሚሆንበት ደረጃ እንዲያመርቱ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል። የምርት ስራቸውን ወደ አዲስ ምርት እንዲያሸጋግሩ ከታሰቡ አምራቾች ውስጥ የአበባ አምራቾች ምርታቸውን ወደ ፍራፍሬ እንዲቀይሩ፣ ጨርቃ ጨርቅ አምራቾች ደግሞ ለኮረና ቫይረስ መከላከያ የሚውሉ እንደ ማስክ ያሉ ምርቶችን እንዲያመርቱ እንደሚደረግ ሚኒስቴሩ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ምርቶች ውስጥ በኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ አጋጣሚ ተፈላጊነታቸው የጨመሩ ቡና፣ እህልና የሰብል ምርቶች ሲሆኑ በአንጻሩ ደግሞ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተፈላጊነታቸው የቀነሰ እና አፈጻጸማቸው ዝቅ ያለ ምርቶች ስጋ፣ ቁም እንሰሳት፣ የኬሚካል ምርቶች፣ ቅመማ ቅመም፣ ጥራጥሬና የቅባት እህሎች መሆናቸውን ሚኒስቴር መሰሪያ ቤቱ አስታውቋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወንድሙ ፍላቴ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት በኢትዮጵያ አሁን ላይ ያለው የውጭ ንግድ ገቢ ያልተቀዛቀዘው የኢትዮጵያን ምርት ተቀባይ ድርጅቶች ችግሩ ሳይፈጠርና ሳይባባስ ቀድመው የገቡት ውል መኖሩ አንዱ ምክንያት መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ነገር ግን ከሚያዚያ ወር ብኃላ አሁን ላይ የታየው የውጭ ንግድ ገቢ የአለም ገብያ መቀዛቀዙን ተከትሎ የኢትዮጵያን ምርት ተቀባይ የሆኑ መዳረሻ አገራት ውል የመሰረዝ እና ቅበላ የመቀነስ አዝማሚያ ሊፈጠር እንደሚችል ስጋታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። እንደ ወንድሙ ገለጻ በወረርሽኙ ሰበብ ተፈላጊነታቸው የጨመሩት የግብርና ምርቶች መሆናቸውንም ታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 77 ሚያዝያ 17 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here