የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 13ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን ሚያዝያ 28/2012 ያደረገ ሲሆን፣ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ምህረት የሚያደርገውን የግብር ማቅለያ መመሪያም አጽድቋል።
የአማራ ክልል ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ እና የክልሉ ገቢዎች ቢሮ በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ከ2007 ጀምሮ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት እየተንከባለሉ የመጡ ወዝፍ እዳዎችን ጨምሮ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በክልሉ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ያጋጠመውን አደጋ ለመቀነስ አዲስ የግብር ከፋዮች የግብር ማቅለያ መመሪያ አዘጋጅቶ በክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት አጽድቋል ብለዋል።
የግብር ማቅለያ መመሪያው ዓላማ ‹ለአንድ ሥራ እኩል ባልደረባን መፍጠር› ያለመ ነው ያሉት የክልሉ ገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ኃላፊ ጥላሁን መሀሪ (ዶ/ር)፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በመንግሥት የሚወሰዱ እርምጃዎችን ውጤታማ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል። በተጨማሪም በእንቅስቃሴ እገዳው የተዘጉ የንግድ ተቋማት እንዳይዘጉ፣ ሠራተኞች ከሥራ ገበታ እንዳይሰናበቱ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አካላት ለበለጠ አደጋ እንዳይጋለጡ እና ወረርሽኙን ለመከላከል ድጋፍ የሚያደርጉ አካላትን ለማበረታታት ያለመ ነው ብለዋል።
በዚህ የግብር ማቅለያ መመሪያ የክልሉ መንግሥት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ምህረት ያደርጋል ያሉት የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ብዙአየሁ ቢያዝን፣ መመሪያው ለአዲስ አሠራር መነቃቃት በር ከመክፈቱ በላይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
መመሪያው በኹለት መንገድ ተፈፃሚ ይሆናል ያሉት ኃላፊው ‹‹እስከ 2007 ያለ የውዝፍ እዳ ሙሉ በሙሉ የሚሰረዝ ይሆናል። ከ2008 ጀምሮ ያለው የግብር ዕዳ ደግሞ መቀጫ እና ወለድ ምህረት ይደረግበታል›› ብለዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 79 ግንቦት 1 2012


