በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጤና ኮሌጅ የሁለተኛ ድግሪ ተማሪ የነበረችው እና ግንቦት 17 ቀን 2012 ዓ/ም በኮሌጁ አስተዳደር ህንፃ ላይ በሚገኘው የላቦራቶሪ ቤተ ሙከራ ክፍል ለምርምር በገባችበት ሁኔታ ህይወቷ ያለፈው ሀይማኖት በዳዳ ገዳይ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ፖሊስ ኮሚሽኑ እንዳለው የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ የሆነውና በ20ዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ደግነት ወርቁ የተባለ ወጣት ነው የ27 ዓመቷን ሃይማኖት በዳዳ ሕይወት ያጠፋው፡፡
ትናንት ምሽት 1 ሰዓት ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት ጋር በመሆን ቀን ከሌሊት ባካሄደው ክትትል ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ሊያውለው መቻሉን አስታውቋል፡፡
ግለሰቡ የ12ኛ ክፍል ተማሪ እንደነበርና የኤች አይ ቪ ኤድስ መድኃኒት ለማግኘት ምርምር ላይ ስለሆንኩ የጥቁር አንበሳ ሐኪሞች ይርዱኝ በማለት ወደ ግቢው በተለያዩ ጊዜያት ይመላለስ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን ከሟች ጋር ምንም ዓይነት ትውውቅ እንዳልነበራቸው ትናንት እስከ እኩለ ሌሊት በተደረገ ምርመራ የወንጀሉን ዝርዝር ለፖሊስ ማስረዳቱም ታውቋል፡፡
በግንቦት 17 ቀን 2012 እንደልማዱ ለዚሁ ጉዳይ እንደመጣ ገንዘብ እንደተቸገረና ቢላዋ ይዞ በግቢው ውስጥ ከሚገኙ ቢሮዎች በአንዱ ላፕቶፕ ወይም ሞባይል ካገኘ ሰርቆ ሽጦ ለመጠቀም ሲዟዟር የሟች ክፍል ክፍት ሆኖ በማግኘቱ መግባቱን አስረድቷል፡፡
በመጀመሪያ ድግሪ ከቴፒ ዩኒቨርስቲ በማዕረግ ተመርቃ በዩኒቨርስቲው ስታገለግል የቆየችው ሀይማኖት በዳዳ ለተጨማሪ ትምህርት ወደ ጥቁር አንበሳ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተልካ ትምህርቷን በመከታተል ላይ ሳለች ግንቦት 17 ቀን 2012 ዓ/ም በኮሌጁ አስተዳደር ህንፃ ላይ በሚገኘው የላቦራቶሪ ቤተ ሙከራ ክፍል ለምርምር በገባችበት ሁኔታ የተለያዬ የሰውነት ክፍሏ በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት ተወግቶ ግንቦት 18 ቀን 2012 ዓ/ም ከቀኑ 11 ሰዓት አስከሬኗ በክፍሉ ውስጥ መገኘቱ የሚታወስ ነው፡፡



