በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት በተደረገ 6187 የላቦራቶሪ ምርመራ ተጨማሪ 170 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው እንዲሁም ተጨማሪ 3 ሰዎች በቫረሱ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።
በዚህም እስካሁን በሀገሪቱ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 2,506 ደርሷል።
ዶክተር ሊያ እንደገለፁት ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው 93 ወንድና 77 ሴቶች ሲሆኑ እድሜያቸውም ከ 2 ዓመት እስከ 115 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ እና በዜግነት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡
ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች 81 ሰዎች ከአዲስ አበባ ሲሆኑ፣
57 ሰዎች ከሶማሊ ክልል፣
13 ሰዎች ከአማራ ክልል፣
7 ሰዎች ከትግራይ ክልል፣
7 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል፣
3 ሰዎች ከሐረሪ ክልል እንዲሁም 2 ሰዎች ከደ/ብ/ብ/ሕ ክልል መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም በቫይረሱ ምክንያት የተጨማሪ 3 ኢትዮጵያዊያን ሰዎች (115 ዓመት ወንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ፣ የ35 ዓመት ወንድ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪ እንዲሁም የ84 ዓመት ወንድ የአዲስ አበባ ነዋሪ) ሕይወት ያለፈ ሲሆን በዚህም በአጠቃላይ በሀገራችን በኮሮና ቫይረስ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር 35 ደርሷል፡፡
በሌላ በኩል በትናንትናው እለት ተጨማሪ 22 ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ 401 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።
ቫይረሱ በሀገራችን እንደተገኘ ከተረጋገጠበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን በአጠቃላይ 158,521 የላብራቶሪ ምርመራዎች የተካሄደ ሲሆን 33 ሰዎች በፅኑ ህሙማን ክፍል ይገኛሉ፡፡





