ኮቪድ 19 የተሰኘው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያልፈተነው የለም። ወረርሽኙ ለአፍሪካም የተፈራላት አስቀድሞም ባልጸና የኢኮኖሚ አቅሟ ላይ ወረርሽኙ ሲጨመር የበለጠ እንደሚያደቃት በመገመቱ ነው። ታድያ በምጣኔ ሀብት ቀዳሚ ተጠቃሽ በሆኑት አገራትም ኢኮኖሚያቸው በዚህ ወረርሽኝ ሳቢያ የተለየ መልክ አሳይቷል። አብርሐም ፀሐዬ ይህን ነጥብ በማንሳት፣ እነዚህ አገራት ያሉበትን የኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲሁም በአገራቱ መካከል ስላለው ግንኙነት በንጽጽር አንስተዋል።
ሰሞኑን የደች ባንኩ ማይክል ስፔንሰር የቻይና ኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚጨምርና የአሜሪካኖቹ ግን ካለበት ፈቅ የሚል አይመስልም ሲሉ ተናግረዋል። የባንኩ ዋና የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ እንደገለጹት፣ በቻይና የአገር ውስጥ ምርት ፍላጎት ከመጨመሩ ጋር ተያይዞ ከሚያዝያ እስከ ሰኔ ባለው ሩብ ዓመት ውስጥ ኢኮኖሚዋን ከ5 እስከ 6 በመቶ ያሳድገዋል ተብሏል።
ከዚያ ቀደም ባሉት ሦስት ወራት ለተጎዳው ኢኮኖሚዋ ይህ መልካም ዜና ነው ተብሏል። የአሜሪካ ኢኮኖሚን በተመለከተ በኮሮና ወረረሽኝ ምክንያት የቢዝነስ እንቅስቃሴው የመከፈት አዝማሚያ ቢያሳይም፣ ድጋሚ ሊከሰት በሚችለው የቫይረሱ ስርጭት የተነሳ ግን ኢኮኖሚዋ የበለጠ አደጋ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል የሚል ስጋት አለ። የሌላውም የዓለም ክፍል ተመሳሳይ ስጋት ላይ የሚወድቅ በመሆኑ አጠቃላይ የዓለማችን ምጣኔ ሀብትም እንደሚላሽቅ አመላካች ነገሮች እየታዩ ነው።
የቫይረሱ ስርጭት ዓለም ዐቀፍ ባህሪን የተላበሰ እንደመሆኑ አንድ አገር ለብቻው የማደግ ዕድሉ አናሳ ነው። በግዢና ሽያጭ የተሳሰረ ንግድ ገዢው ባይጎዳ ሻጩ፣ ወይም ደግሞ በተቃራኒው የንግድ ሰንሰለት ውስጥ ስለሚገቡ ጉዳቱ ጠቅላላ የዓለም አገራት ላይ ጫናውን ማሳረፉ ግልጽ ሆኗል።
ማይክል ስፔንሰር ምናልባት የአሜሪካ ኢኮኖሚ ከኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በፊት በነበረው የምጣኔ ሀብት ዕድገት ደረጃ ላይ ልትሆን እንደማትችል ገልጸው፣ ይህ ችግርም እስከ 2022 እንደሚቆይ ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል። እንደውም ከዚያ በላይም ሊጓዝ ይችላል የሚል ትንተና አላቸው።
በቻይና በኩል ግን የአገር ውስጥ ፍላጎት መሻሻሉ እንዳለ ሆኖ የመኪኖችና ሌሎች ቁሳቁሶችም ወደ ውጭ ገበያ እየቀረቡ በመሆናቸው ተስፋ ሰጪ ምልክቶች እየታዩ ነው ብለዋል። የእነዚህ ገበያዎች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ መግባት መልካም ዜና ሆኖ፣ መዳረሻ የሆኑ አገራት ላይ ከቫይረሱ ስርጭት ጋር ተያይዞ ባለው ስጋት የቻይና ብቻ ጥሩ መሆን ብቻውን ፋይዳ ላይኖረው ይችላል። ይህ ስጋትም በሚቀጥሉት ወራት እንደሚቀጥል ጭምር ተተንብይዋል።
የአሜሪካና ቻይና የምጣኔ ሀብት ዕድገት ንጽጽር
የዓለም ግዙፍ የምጣኔ ሀብት ባለቤት አሁንም አሜሪካ ናት። ይህንንም በ20.9 ትሪሊዮን ዶላር ስትመራ፣ ቻይና ደግሞ በ13.4 ትከተላለች። በምጣኔ ሀብቱ ከአንድ እስከ አስር ደረጃ ውስጥ ያሉትን አገራት ብንመለከት፣ ሁሉም በትሪሊዮን ዶላር የሚመነዘር ሀብት አላቸው።
የአምስቱን ደረጃ እንመልከት (Nominal GDP Rankings by Country)
አሜሪካ (20.49 )
ቻይና (13.4)
ጃፓን (4.97)
ጀርመን (4.00)
እንግሊዝ (2.83)
ከእነዚህ አገራት ውስጥ ግንባር ቀደም የሆኑት አሜሪካና ቻይና የዓለም ምጣኔ ሀብትን ግራና ቀኝ አቁመው የያዙ ኃያላን ናቸው።
አሜሪካ
አሜሪካ ከ1871 ጀምሮ የዓለምን ምጣኔ ሀብት የተቆጣጠረች ክንደ ብርቱ አገር ናት። አገሪቷ በገነባችው የምጣኔ ሀብት ስርዓት ጫፍ ላይ መገኘቷ እንዳለ ሆኖ፣ በተፈጥሮ ሀብትም እንዲሁ በኹለተኝነት ደረጃ ላይ ትገኛለች። አገረ አሜሪካ ለዚህ ያበቋት በርካታ እሴቶች ያሏት ሲሆን፣ ዜጎቿ ወደ ሥራ ፈጠራ እንዲገቡ ከፍተኛ ድጋፍ የምታደርግ በመሆኗ እንደሆነ ይነገርላታል።
ከዚህ በተጨማሪም ለማኑፋከችሪንግ ዘርፉ የምትሰጠው ትኩረት፣ የሕዝብ ስብጥሯ ከተለያዩ አገራት በመጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንደመዋቀሩ፣ ይህ በራሱ ለዕድገቷ ግብዓት እንደሆናት ይታመናል። ከዚህ በተጨማሪ የገንዘብ ኖቷ በአብዛኛው የዓለም ክፍል ተጽእኖ ፈጣሪ በመሆኑ የተነሳ ለምጣኔ ሀብቱ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጎላታል።
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የአሜሪካ በኮቪ 19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መጠቃት እና በቅርቡ ደግሞ የጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድን ኢ-ሰብአዊ አሟሟት ተከትሎ፣ የመጣው ተቃውም የሥራ እንቅስቃሴዎቿን እያወከው ይገኛል። ይህ ክስተት ዕድገቷ በተፈለገው ፍጥነት ወደፊት እንዳይራመድ እግር ከወርች ያሰራት ቢሆንም፣ ቀድማ ከገነባችው የኢኮኖሚ ስርዓት አንጻር ግን ካለችበት ወደታች የሚያሽቆለቁል ከፍተኛ ስጋት የለባትም።
ቻይና
ባለኹለተኛው ግዙፍ የምጣኔ ሀብት ባለቤት ቻይና ስትሆን፣ በተለይ ከ1989 – 2019 ባሉት ዓመታት በአማካይ 9.52 ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች እዚህ ደርሳለች። ቻይናም በተለይ በብረትና ከሰል የታደለ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ናት።
አገሪቷ በ1979 ያካሄደችው የኢኮኖሚ ማሻሻያ የኢኮኖሚ ዕድገቷ ከስድስት በመቶ ወደ ዘጠኝ በመቶ ማደግ ሲችል በግል ሥራ ፈጠራ፣ በገጠር የንግድ ሥራዎች ላይ፣ በሸቀጥና አገልግሎት ዋጋ ማሻሻያ፣ የዜጎችን የሥራ አቅም በማጎልበት፣ ትምህርትና ኢንዱስትሪን በማስፋፋት በኩል ያደረገችው ማሻሻል ለዚህ ዕድገት አብቅቷል።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭት መነሻ የሆነችው ቻይና፣ ስርጭቱን በትልቅ ርብርብ መቀነስ ብትችልም በዓለም ዙሪያ የተሰራጨው ቫይረስ ግን በምጣኔ ሀብት ብቻ ሳይሆን ከአሜሪካም ጋር እንካ ሰላምታ በመፍጠር በፖለቲካና የንግድ እንቅስቃሴያቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያመጣባት ይገኛል። ያም ሆነ ይህ ግን ለጊዜው ያለው እውነታ ከአሜሪካ አንጻር የተሻለች እንደውም እንደዚህ ቀደሙ ሳይሆን ዕድገት እንደምታስመዘግብ ታውቋል።
የሉላዊነት ፈተና በኮቪድ 19 ወረርሽኝ
የኮሮና ወረርሽኝ በአገራት መካከል ያለው ትስስር ምን ያህል ጥብቅ እንደሆነና አስፈላጊነቱንም ጭምር አሳይቷል። በ21ኛው ክፍለ ዘመን የዓለም የምጣኔ ሀብት ዕድገት በንጽጽር የተሻለ ደረጃ ላይ መገኘት ዋናው ምክንያት ዓለም ቅርርቧን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠበቀች በመምጣቷ የተነሳ ነው። ሉላዊነት (Globalization) የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ማቀነባበሪያ ነው እያሉ አሉታዊ ጎኑን የሚናገሩለት እንዳሉ ሆነው፣ የዓለም አገራት መቀራረብ የተሻለች ዓለም ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገ የሚያምነው ይበረክታል።
የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የግብዓትና ያለቀላቸው ምርቶች ግብይት፣ የዕውቀትና ክህሎት መዳረስ የመሳሰሉት ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል። በዚህም ቢያንስ የሰው ልጅ በተሻለ የአኗኗር መንገድ እያለፈ ነው ማለት ይቻላል በሚል ማሳያ የሚያቀርቡ አሉ።
ይህ ሉላዊነት ያመጣው ሌላው ነገር ምንድነው ቢባል፣ አንዱ ቦታ የሚፈጠረው ችግርም ሆነ መልካም ነገር እዚያው ባለበት አለመቅረቱ ነው። እንደሚታወቀው አፍሪካ ላይ ያለው አለመረጋጋት አውሮፓን በስደተኞች ሊረብሻት ይችላል። የውጭ አገራት ኩባንያዎች ሊጎዱ ይችላሉ። ከኮሮና ጋር ተያይዞም ተመሳሳይ ክስተት ነው። የበሽታው ስርጭት በቻይና እንደተፈጠረ ሳይቀር ዓለማቀፋዊ አድርጎታል።
በሁሉም ዘርፍ ትስስሩ የዘለቀ ነው። ለዓለምም ሆነ ለቻይና ምጣኔ ሀብት መልካም መሆን ወይም ችግር መከሰት የአሜሪካ የምጣኔ ሀብት ጉዳይ ትልቅ ሚና አለው። በኹለቱ መካከል ያለው ግብይት ግዙፍ ከመሆኑ የተነሳ አንዱ አገር ደኅና ሆኖ ሌላው ጤነኛ መሆን አይችልም። ስለሆነም አሜሪካ ባልቀረፈችው ችግር የተነሳ ዓለም መጎዳቷ እሙን ነው። ቻይና እና አሜሪካ ተፎካካሪነታቸው እንዳለ ቢሆንም፣ ከፍተኛ የገበያ ትስስር እየፈጠሩ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚፈላለጉበት መንገድ ሰፊ ነው።
የኮቪ 19 ወረርሽኝ እውነታ እንዳለ ነው። ስፔንሰር በበኩላቸው ‹‹አሜሪካ ከገባችበት የምጣኔ ሀብት አረንቋ ለመውጣት ቀላል የማይባል ዓመታት ይወስድባታል።›› ብለዋል። ቻይና ደግሞ ለጊዜው ዕድገቷ አልተጎዳም እንደውም የኢኮኖሚ ዕድገቷ እንደሚቀጥል ተተንብይዋል። ወደፊት ደግሞ የሚሆነውን እናያለን።
እዚህ ጋር የሚነሳ ነጥብ አለ። ቻይና ማደጓ ብቻውን ፋይዳ ከሌለው፣ አሜሪካም ዕድገቷ ከፍ አለማለቱ ምናልባት እሷን ባይጎዳም የሌላው ዓለም ክፍልን ታሳቢ ያላደረገ ማንኛውም ዕቅድና እንቅስቃሴ ዋጋ አይኖረውም። አሜሪካ ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ያዘጋጀችው ‹ማርሻል ፕላን› አውሮፓን ወደተሻለ የምጣኔ ሀብት ዕድገት በማምጣት ዓለም ከአጠቃላይ የኢኮኖሚ ቀውስ እንድትድን ያገዘ ነበር። አሁንም ደሀ አገራት በዚህ ወረርሽኝ ምክንያት ከሚደርስባቸው ቀውስ የሚድኑበት ዕቅድ እንዲዘጋጅ እየተጠየቀ ያለው ለዚህ ነው። መውደቅና መነሳት አብሮ ስለሆነ።
ቸር ወሬ
ያም ሆነ ይህ ዓለም ስለራሷ ስትል መፍትሄ መሻቷ ግድ ይላታል። ለዚህም ነው አንተኒ ፋውቺ ለወረርሽኙ ክትባት እንደሚገኝ አጠንክረው የተናገሩት። እኚህ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የጤና ጉዳዮች አማካሪ የቫይረሱ ወረርሽኝ ገና እንዳልወጣለት ተናግረዋል። ምንም እንኳን ቫይረሱ በከፍተኛ ፍጥነት መስፋፋት ቢያሳስባቸውም፣ ክትባቱ ግን መፍትሄ እንደሚገኝለት እርግጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። ቸር ያሰማን!
አብርሐም ፀሐዬ የቢዝነስ አማካሪና ጋዜጠኛ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ላይ ይገኛሉ።
ቅጽ 2 ቁጥር 84 ሠኔ 6 2012



