የአፍሪካ አገራት ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከተያዘለት ጊዜ በመራዘሙ እ.ኤ.አ 2021 ጥር ወር ላይ እንዲጀመር አቅጣጫ መቀመጡ ተጠቆመ።
የአፍሪካ አገራት የመሠረቱት ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ ቀድሞ በተደረሰው ስምምነት በታቀደለት ጊዜ መሠረት በአውሮፓውያኑ 2020 ሐምሌ 1 ወደ ትግበራ ሊገባ የነበረ ቢሆንም፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋት ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ መሸጋገሩን ተከትሎ የትግበራ ጊዜ ገደቡ በሚቀጥለው በኢትዮጵያ አቆጣጠር 2013 ጥር ወር ላይ እንዲጀመር ቀን እንደተቆረጠለት ታውቋል።
የቀጠናው ነፃ ንግድ ሐምሌ 1/2012 ለማስጀመር የተቀመጠ እቅድ በቀጣይ ወር ለማስጀመር በአገራቱ መካከል የሚደረጉ ቅድመ ድርድሮችና ስምምነቶች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት መካሄድ ባለመቻላቸው እንደተራዘመ በንግድ ሚኒስቴር የሁለገብ ንግድ ግንኙነት ዳይሬክተርና በአፍሪካ ነፃ ንግድ የአትዮጵያ ረዳት ተደራዳሪ ሙሴ ምንዳ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ጁሀንስበርግ ላይ የሚደረገውን የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ እና ሌሎች ድርድሮች ለማካሄድ ባለመቻሉ የድርድር ስብሰባዎችን በኢንተርኔት አማካኝነት ከዚህ ወር ጀምሮ እንደሚደረጉ ሙሴ ጠቁመዋል። ነገር ግን የመሪዎችን ስብሰባ በሚመለከት በኢንተርኔት ማድረግ እንደማይቻል ሙሴ አመላክተዋል። በዚህም ምክንያት የመሪዎቹ ስብሰባ የሚደረግበት ጊዜ የቀጠናን ነፃ ንግድ በቀጣይ ጥር ወር መጀመሩን የሚወስነው ይሆናል ተብሏል።
የቀጠናው ነፃ ንግድ ስምምነት ለታዳጊ አገራት ለአምስት ዓመት 90 በመቶ የሚሆነውን ግብይታቸውን፣ ለዝቅተኛ ታዳጊ አገራት ለዐስር ዓመት 90 በመቶ ግብይታቸውን እንደሚሆን ሙሴ ተናግረዋል። አገራቱ ዐስር በመቶ የሚሆነውን ምርታቸውን ከቀረጥ ነፃ አለማድረግ የስምምነቱ አካል በመሆኑ፣ ኢትዮጵያም ዐስር በመቶ የሚሆነውን የንግድ ግብይቷን ነፃ የማታደርጋቸውን ዘርፎች እያጠናች መሆኑን ሙሴ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በቀጠናው ነፃ ንግድ ትግበራ ከዚህ በፊት ከአፍሪካ አገራት ጋር የነበራትን አነስተኛ የግብይት ግንኙነት ወደተሻለ ገብያ ዕድል ከፍ እንደሚደረግላት የሚጠበቅ መሆኑን ሙሴ ገልጿል። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላት ገቢ ንግድ ከአጠቃላይ ገቢ ንግዷ 4 ነጥብ 6 በመቶ ብቻ ሲሆን፣ ነፃ ንግዱ ይሄንን ችግር እንደሚፈታ ሙሴ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በነፃ ንግዱ ትግበራ ኢትዮጵያ በዓመት 920 ሚሊዮን ብር ገቢ እንደምታጣ ተጠቁሟል። እንዲሁም የመንግሥት ገቢ እንደሚቀንስ ሙሴ አመላክተዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ በነፃ ንግዱ የአጭር ጊዜ ተጠቃሚ ላትሆን ትችላለች፣ ነገር ግን ኢንቨስትመንቱ እያደገ ሲሄድ የረጅም ጊዜ ተጠቃሚ እንደምትሆን ተመላክቷል።
በቀጠናው የነፃ ንግድ ስምምነት ትግበራ ማግስት በዘላቂነት ሁሉንም የአፍሪካ አገራት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ በተሠሩ ጥናቶች መመላከቱን ሙሴ ተናግረዋል። ከአገራቱ ውስጥ እንደ ሞሮኮ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ የተሻለ አቅም ያላቸው አገራት ከሌሎች የአፍሪካ አገራት በተሻለ በአጭር ጊዜ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተጠቁሟል።
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ባላት አኅጉር የሚደረግ የንግድ እንቅስቃሴ ነው። በጥቅል አኅጉራዊ ምርት እስከ 2 ነጥብ 5 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ የንግድ እንቅስቃሴም የሚከወንበት ነው።
የነፃ የንግድ ቀጣናው በአፍሪካ ኅብረት መሪነት ወደ ትግበራ ለመግባት በሂደት ላይ ይገኛል። ስምምነቱ የበለጸጉ አገራት በአምስት ዓመት፣ ታዳጊ አገራት ደግሞ በዐስር ዓመት ነፃ የንግድ ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ እንዲተገብሩ የሚጠይቅ ነው።
በአፍሪካ የሸቀጦች፣ የአገልግሎቶችና የሰዎች ዝውውር ነፃ መሆን በርካታ ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩት ይጠበቃል።
የአፍሪካ ወጭና ገቢ ንግድ ባንክ ትንበያ እንደሚያመለክተው ነፃ የንግድ ቀጣናው ሲተገበር የእርስ በእርስ የንግድ ትስስሩን በአንድ ዓመት ውስጥ ወደ 52 በመቶ ያሳድገዋል፤ በዐስር ዓመታት ውስጥም በእጥፍ ያድጋል ሲል ያትታል።
ቅጽ 2 ቁጥር 84 ሠኔ 6 2012



