የፀሐይ ግርዶሹን ያለመመልከቻ መነጽር መመልከት የዐይን ብርሃንን ሊያሳጣ እንደሚችል የኢትዬጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቱ አስጠነቀቀ።
የፊታችን እሁድ ሰኔ 14/2012 በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ፀሐይ ከ60 እስከ 80 በመቶ ተሸፍና ከፊል ግርዶሽ ይታያል ተብሎ ይጠበቃል።
ከ80 በመቶ በላይ ያለው ዋናው ግርዶሽ ግን ከምዕራብ ኢትዮጵያ አንሥቶ እስከ ሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ በሚገኙ ቦታዎች ጎልቶ እንደሚታይ ኢንስቲትዩቱ ሰኔ 11/2012 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።
በመግለጫው እንደተመለከተው ክስተቱ ከወለጋ አካባቢ ጀምሮ ከፊል ጎጃም እና ከፊል ጎንደርን አልፎ ከዚያም ላሊበላን አቋርጦ ይሄዳል። በእነዚህ ቦታዎች ፀሐይ እስክ 99 በመቶ ተሸፍና ቀለበታዊውን ግርዶሽ ማየት እንደሚቻልም ነው የተገለጸው።
ቀለበታዊ ግርዶሽ ማየት ከሚችሉ አነስተኛ ከተሞች (ቦታዎች) መካከል ቡሬ፣ አገው ግምጃ ቤት፣ እንጅባራ፣ ግሽ አባይ፣ ሞጣ፣ ዳሞት፣ ጋይንት፣ ነፋስ መውጫ፣ ጋሸና፣ ሙጃ፣ ዋጃ፣ ቆቦ፣ ኮረም፣ አላማጣ፣ ጊራራ እና ላሊበላ ይገኙበታል።
በአዲስ አበባ፣ ሐዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ መቀሌ፣ ደሴ፣ አዳማ፣ ቤጊ፣ ሜቲ፣ መንዲ፣ ጫልቱ፣ በመሳሰሉት ከተሞች ደግሞ ቀለበታዊ ግረዶሽ ባይኖርም ከፊል የፀሐይ ግርዶሽ ግን እንደሚኖራቸው በመግለጫው ተመላክቷል።
ግርዶሽ ሲፈጠር ክፍተኛ ሃይል ከፀሐይ ሊረጭ ስለሚችል በባዶ ዐይን ማየት ለችግር እንደሚጋልጥ ያመላከተው መግለጫው ማኅበረሰቡ ጥንቃቄ በማድረግና መነጽር በመጠቀም የታሪኩ አካል መሆን እንዳለበትም አስታውቋል።
ወቅቱ የኮሮና ባይሆን ኖሮ ክስተቱን ለመመልከት ከ20 ሺህ በላይ ጎብኝዎች ተመዝግበው እንደነበር በማመላከትም ይህ ደግሞ በዓለማችን ላይ ውድ ቱሪዝም የሆነው የስፔስ ቱሪዝም አካል ያደርገን እንደነበር ነው የተገለጸው።
ቅጽ 2 ቁጥር 85 ሠኔ 13 2012



