የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት በዘመነ ኮሮና

0
1470

የዛሬ ሦስት ወር ገደማ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የኮሮና ቫይረስ ታማሚ ይፋ ሲደረግ ዜጎች በቤታቸው በመቆየት የቫይረሱን ስርጭት መግታት እንደሚገባቸው የጤና ሚኒስቴር አሳስቦ ነበር። ምንም እንኳን የቫይረስ ስርጭት አሁን እንዳለበት ሁኔታ ተስፋፍቶ የነበረ ባይሆንም፣ ብዙዎች የሚኒስቴሩን ምክር ተቀብለው ቤታቸው ተቀምጠው ሥራቸውን መሥራትን መርጠው ነበር።

በአንድ ዓለም ዐቀፍ ተቋም በግራፊክስ ዲዛይነርነት ተቀጥሮ የሚሠራው ቴድሮስ ዓለሙ የቤታችሁ ተቀመጡ ምክርን ተግባራዊ ካደረጉ ዜጎች አንዱ ነበር። ኧረ እንደውም ቤቴ ተቀመጬ ልሥራ የሚል ጥያቄ ለአለቃው ሲያቀርብ ወዲያውኑ ነበር አዎንታዊ ምላሽ ያገኘው። ይሁን እንጂ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ለሚኖረው ቴድሮስ ከቤት ተቀምጦ የተሰጡትን ሥራዎች ማከናወን እንዳሰበው ቀላል ሊሆንለት አልቻለም።

በተደጋጋሚ መብራት መጥፋቱ፣ ከዚያም ለቀናት ቴድሮስ የሚኖርበት አካባቢ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ትራንስፎርመር በመበላሸቱ ምክንያት በመቋረጡ ሥራውን እንዳሰበው እንዳይሠራ እንቅፋት ሆኖበት ቆይቷል። ‹‹ለአምስት ቀናት ሙሉ ለሙሉ መብራት በመጥፋቱ ምክንያት ስልኬን እንኳን ቻርጅ ማድረግ አልቻልኩም፤ እንኳንስ የተሰጡኝን ሥራዎች ላከናውን ቀርቶ›› ይላል ቴድሮስ ያገጠመውን ሲያስረዳ።

ቴድሮስ እና ጎረቤቶቹ መብራት እንደጠፋባቸው ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሪፖርት ቢያደርጉም የአካባቢያቸውን ኤሌክትሪክ ወደ ዘረጋው ፕሮጀከት ቢሮ እንዲሄዱ ተነግሯቸዋል። በድጋሚ የፕሮጀክት ቢሮ ደግሞ እንደማይመለከታቸው በመግለፅ ተመልሰው አገልግሎቱን እንዲጠይቁ ይነግራቸዋል።

‹‹የመብራት መቆራረጥ እና ሙሉ ለሙሉ መጥፋቱ እኔን በአለቃቼ ዘንድ ቃላባይ ከማድረጉ በላይ የሚያሳዝነው እንዲሠራልን ባመለከትን ወቅት የገጠሙን ፈተናዎች ናቸው።›› አንዱ አንዱን መንግሥት መሥሪያ ቤት፣ ሌላውም ሌላኛውን፣ እየተወነጃጀሉ ለጥገና እንኳን ሲደወልላቸው ሊመጡ አልቻሉም ነበር።

‹‹የበለጠ የሚያሳዝነው ብዙዎቹ የመብራት ጠጋኞች ጉቦ በመልመዳቸው ገንዘብ ለሚሰጧቸው ጥሩ የሚባል አገልግሎት ሲሰጡ፣ ለሌሎች ደግሞ የይድረሰ ይድረሰ ሥራ ሠርተው ነው የሚሄዱት›› ይላል ቴድሮስ ከቤት ውስጥ መሥራት ለኢትዮጵያውያን የማይታሰብ መሆኑን በማንሳት።

መብራት መጥፋት እና መቆራረጥ ለኢትዮጵያውያን አዲስ ነገር አይደለም። በከተማም ሆነ በገጠር የሚኖሩ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ ኢትዮጵያውያን መብራት ሳያገኙ ሳምንት ወይም ከሳምንት በላይ ሊቆዩ ይችላሉ። ምንም እንኳን እንደ አዲስ አበባ ባሉ ትላልቅ ከተሞች የመብራት መቆራረጥ ቀነስ ያለ ቢሆንም፣ በሳምንት ከኹለት ጊዜ በላይ ሳያጋጥመው የማያልፍ ነዋሪ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ይባስ ብሎ፤ ሙሉ ለሙሉ አገሪቷ በጨለማ የተዋጠችባቸው ወቅቶች ነበሩ። ለአብነትም በጥር 2012 በመላው አገሪቷ በሚባል ደረጃ የተከሰተውን የመብራት መጥፋት ማንሳት ይቻላል። በወቅቱ 1870 ሜጋዋት የሚያስተላልፈው የጊቤ ሦስት ኃይል ማስተላለፊያ ሰርኪዩት ብሬከር በመበላሸቱ የተነሳ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፣ ችግሩንም ለመፍታት ከስድስት ሰዓታት በላይ ፈጅቶ ነበር።

ምናልባት ባደጉት የዓለም አገራት ይህ ቢያጋጥም ከፍተኛ ኪሳራ ከማስከተለም በላይ የመንግሥት ቅቡልነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር ክስተት ሆኖ ሊያልፍ ይችል ነበር። ቢሆንም ለኢትዮጵያውያን ይህ አይነቱ አጋጣሚ ምንም አይገርምም። ኧረ እንደውም በአንዳንድ የክልል ከተሞች የጥገና አገልግሎት የሚሰጡ ሠራተኞች ባለመገኘታቸው ከሳምንት በላይ የመብራት መቋረጥ ሊያጋጥም ይችላል።

የተበላሹ የኤሌክትሪክ መስመሮች እንዲሁም ትራንስፎርመሮችን ለማስገጠም የጥገና አገልግሎት ማግኘት፣ ለማግኘት ከባድ ከሚባሉ አገልግሎቶች ዘንድ እንደ አንዱ ሲነሳ በብዛት ይሰማል። ለአብነትም ባለፉት ሦስት ወራት ቦሌ ክፍለ ከተማ ሰዓሊተምሕረት ቤተክርስትያን አካባቢ በሃኮማል ኮንስትራክሽን መኖሪያ መንደር ያጋጠመውን ማንሳት ይቻላል።

ከ100 በላይ የሚሆኑ አባውራዎች በሚኖሩበት መኖሪያ መንደሩ ነዋሪዎቹ ከኹለት ወር በላይ በመብራት ዕጦት እየተንገላቱ ሲሆን፣ ችግሩ እንዲፈታላቸው በተደጋጋሚ ወደ ሚመለከተው አካል በመቅረብ ቢጠይቁም እስከ አሁን ድረስ መፍትሔ አላገኙም።

ምንም እንኳን ነዋሪዎቹ የመብራት ኃይል ኃላፊዎችን መልስ እንዲሰጧቸው ለወራት ቢጠይቁም፣ መልስ ባለማግኘታቸው ሐኮማል አፓርትመንት ባቀረበው አማራጭ በቀን ለሰባት ሰዓት ብቻ በጀነሬተር መብራት ለማግኘት ለ10 ቀን 500 ብር እንዲከፍሉ ተጠይቀው፣ በድርድር ለ10 ቀን 300 ብር እየከፈሉ ላልተፈለገ ወጭ እየተዳረጉ መሆኑን በምሬት ይናገራሉ።

የመብራት አገልግሎት መቶ በመቶ በተዳረሰበት አዲስ አበባ ይህን አይነት ችግር ከገጠመ በሙሉ በመላው አገሪቷ ከዚህ የባሰ ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። በእርግጥ አፋጣኝ የጥገና አገልግሎትን እንደ ማግኘት ከባድ ነገር የለም። የመብራት ኃይል ባለሥልጣናትም በአፋጣኝ ምላሽ ባለመስጠት በቀዳሚነት ከሚታሙ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች መካከል ናቸው ቢባል ማጋነን አይደለም።

ከዚህ ባሻገር አዲስ አገልግሎት ጠያቂዎችም ቆጣሪ ማስገባት ቢፈልጉ ረጅም ሰልፎችን መጠበቅ ሊኖርባቸው ይችላል። ምን ይሄ ብቻ! አገልግሎቱ የመብራት ቢል ክፍያን ዲጂታይዝ ለማድረግ ሙከራዎችን ቢያደርግም፣ አሁንም ተገልጋዮች የተጠቀሙበትን ለመክፈል ሲቸገሩ ማየት የተለመደ ነው።

ከሁሉም በላይ ችግሩን አሳሳቢ ያደረገው ነገር ቢኖር በኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ወቅት መረጃ ማግኘት አስፈላጊ ቢሆንም፣ በመብራት መቆራረጥ እና መጥፋት ምክንያት ብዙዎች እንደ ቴሌቭዥን እና ሬዲዮ ያሉ የመገናኛ ብዙኀንን እንዲሁም በሞባይላቸው ማኅበራዊ የትስስር ገጾችን መከታተል ያለመቻላቸው እንደሆነ ይነሳል።

‹‹የመብራት አገልግሎት ለኹለት ወራት በመኖሪያ አካባቢዬ በመጥፋቱ ቲቪ ላይ የሚተላለፉ መረጃዎችን መከታተል አልቻልኩም። አንዳንዴም በቀን ምን ያህል ሰዎች እንደተያዙ እና በመንግሥት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎችን ሳላውቅ የሚነጋበት ወቅቶች ትንሽ አልነበሩም›› ሲሉ አንድ በፊጋ አካባቢ መብራት ለኹለት ወር ያላገኙ ነዋሪ ያነሳሉ።

ይህ አይነቱ ተሞክሮ መንግሥት በኮሮና ወቅት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ዜጎች በፍጥነት እና በሰዓቱ መረጃ ማግኘት ይገባቸዋል ከሚለው ጋር የሚፃረር ነው። ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ ችግሩ የተከሰተው ከአቅም በላይ በሆኑ ምክንያቶች እንደሆነ ያነሳል።

የመብራት ፍጆታ በዘመነ ኮሮና
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ አንስቶ የአገሪቷ ዜጎች በቤታቸው የተጠቀሙት የኤሌክትሪክ ፍጀታ መጋቢት 2011 ላይ 371 ኪሎዋት ሃወር የነበረ ሲሆን፣ በቀጣይ ወር ወደ 379 ኪሎዋት ሃወር አድጎ ነበር። በሌላ በኩል ኢንዱስትሪዎች በቫይረሱ ምክንያት በመዘጋታቸው ወርሃዊ ፍጆታቸው በተመሳሳይ ወቅት በ27 በመቶ ወርዶ የነበረ ሲሆን፣ የንግድ ተቋማት ፍጆታ ደግሞ በ70 በመቶ ወርዶ 707 ኪሎ ዋት ሃወር ደርሶ ነበር።

ከቁጥሩ መረዳት እንደሚቻለው፣ በኮሮና ቫይረስ ወቅት የቤት ተጠቃሚዎች ፍጆታ ያደገ ሲሆን የንግድ ተቋማት እና የኢንዱስትሪ ፍጆታ ግን ከፍተኛ ቅናሽ አሳይቷል። ‹‹በቫይረሱ ምክንያት ዜጎች ማኅበራዊ ርቀትን ለመጠበቅ ሲሉ በቤታቸው በመቀመጣቸው የኤሌክትሪክ ፍጆታቸው ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል›› ሲሉ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዋና አማካሪ የሆኑት ሕዝቅያስ ዱፌራ ያነሳሉ። በዚህም የተነሳ ከቫይረሱ በፊት ከፍተኛ የኃይል ፍጆታ የሚኖረው ምሽት ላይ እና በእረፍት ቀናት የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ሁሌም የሚታየው መጠን ከፍተኛ እንደሆነ ሕዝቅያስ ያነሳሉ።
በሌላ በኩል የኢንዱስትሪዎች ፍጆታ ቢቀንስም ፍላጎት እንዳልቀነሰ የዘርፉ ተዋንያን ጠቅሰዋል። በተለይም በኮቪድ 19 ወቅት አስፈላጊ የሆኑ መሰረታዊ ምርቶችን ኢንዱስትሪዎች በኃይል እጥረት የተነሳ ማምረት አለመቻላቸውን ያነሳሉ። ለአብነትም በ6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በቡሬ እና በደብረማርቆስ በመገንባት ላይ ያሉትን የዘይት ፋብሪካዎችን ማንሳት ይቻላል።

የዘይት ፋብሪካዎቹ ከአገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለውጭ ገበያ ምርት ለማቅረብ ታላሚ ተደርገው የተገነቡ ቢሆንም፣ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ማግኝት ባለመቻላቸው ወደ ሥራ ሊገቡ አለመቻላቸውን በቅርቡ ይፋ ተደርጎ ነበር።

በተመሳሳይ በአማራ ክልል ከ350 ኢንዱስትሪዎች በኃይል አቅርቦት ምክንያት በሥራ ላይ መግባት አለመቻላቸውን የክልሉ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የኤሌክትሪክ ንዑስ ጣቢያዎች ቁጥር አነስተኛ መሆን እና የኃይል መሸከም አቅማቸው ደካማ መሆኑ ተነስቷል።

የተለያዩ በፍጥነት የሚያልቁ የፍጆታ ምርቶችን በማምረት የሚታወቀው ኢስት አፍሪካን ሆልዲንግስ ያጋጠመውም ከዚህ ብዙም የተለየ አይደለም።
‹‹ምንም እንኳን የውጭ ምንዛሬ እና የጥሬ ዕቃዎች እጥረት የማምረት አቅማችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ቢያሳድሩብንም፣ የኃይል አቅርቦት ያለ ማቋረጥ ብናገኝ ኖሮ ምርታማነታችንን በመጨመር በተመጣጣኝ ዋጋ የተለያዩ አላቂ ምርቶችን ማቅረብ ያስችለን ነበር›› ይላሉ፤ የኢስት አፍሪካን ሆልዲንግስ ቺፍ ኦፍ ስታፍ ፍፁም ደጀኔ።

በኢትዮጵያ ከሚመረተው ዘጠኝ ሺሕ ጊጋዋት ሃወር ኤሌክትሪክ ኃይል ወደ 96 በመቶ የሚሆነው የሚገኘው ወንዞች ላይ ከተገነቡ ግድቦች ሲሆን፣ ቀሪው ከንፋስ፣ ከሶላር አና ከጂኦተርማል ኢነርጂ ነው። በተጨማሪ ከሚመረተው አጠቃላይ ኃይል ውስጥ ወደ 11 በመቶ የሚሆነው ወደ ውጪ ይላካል። ወደ 20 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በስርጭት ወቅት የሚባክን ሲሆን ቀሪው ለአገር ውስጥ ፍጆታ ይውላል።

በተጨማሪ የአገር ውስጥ ፍጆታ ከሕዝብ ቁጥር መጨመር እና ከኢንዱስትሪዎች መስፋፋት እንዲሁም ከከተሞች መስፋት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ዕድገት ያሳያል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በየዓመቱ ወደ 12 በመቶ ዕድገት ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል።

መብራት እጦትን እንዴት መፍታት ይቻላል?
መንግሥት ባለፉት 15 ዓመታት የመብራት ሽፋንን ለማሳደግ በርካታ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድቦችን እንዲሁም የንፋስ እርሻዎችን እና ሌሎች የኃይል ማመንጫዎችን ገንብቷል። ይህንንም በማድረግ የዛሬ 27 ዓመት በፊት ወደ 380 ሜጋ ዋት የነበረውን የአገሪቷ ኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ወደ 4,514 ሜጋ ዋት ማሳደግ ችሏል።
ይህም ከሰሀራ በታች ባሉ አፍሪካ አገራት ካላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት አቅም ጋር አንፃር ኢትዮጵያ ኹለተኛ ደረጃ እንድትይዝ አድርጓታል።

በተጨማሪ ባለፉት ኹለት ዐስርት ዓመታት በተደረገው የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ፣ በከተሞች ከ90 በመቶ የሚሆኑ አባወራዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያገኙ ሲሆን በገጠር ያለው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽፋን ግን ከ27 በመቶ አይዘልም። ታዲያ አገልግሎቱን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰደ ሲሆን አንዱ አገር አቀፍ የኤሌክትሪክ ፕሮግራም ነው።

የኤሌክትሪክ ሽፋን 75 በመቶ ለማድረስና በአጠቃላይ በአገር ደረጃ 10,164 ከተሞች፣ መንደሮችና የገጠር ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል በአገር አቀፍ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም በመተግበር ላይ ነው። የማሰራጫ ኔትዎርክ ግንባታ እንዲሁም የማከፋፈያና የማስተላለፊያ መስመር ግንባታዎችም እየተሠሩ ይገኛሉ።

እነዚህን ሥራዎች ለማሳካት እንዲሁም የተቀመጠውን ግብ ለመምታት የአገር ዐቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም አደረጃጀትን ወደ ያልተማከለ አደረጃጀት የሚደግፍ የአሠራር ማሻሻያ ሥርዓት በ2006 በስምንት ክልሎች ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፣ 74 የወረዳ ማስተባበሪያ ቢሮዎች ወደ ሥራ ገብተዋል። በተጨማሪ ኹለተኛው የአገር ዐቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም ከባለፈው ዓመት አንስቶ ተግባራዊ መደረግ የጀመረ ሲሆን፣ ወደ ስድስት ቢሊዮን ዶላር አካባቢ በስሩ የታቀዱትን ፕሮጀክቶች ለመፈፀም ያስፈልጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ምንም እንኳን ይህንን ተግባራዊ በማድረግ መንግሥት የኤሌክትሪክ ሽፋንን ለማሳደግ እየሠራ ቢሆንም፣ አሁንም በተግባር እየዋለ ያለው ፖሊሲ መሬት ላይ ያለውን ችግር ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ይላሉ፤ ባለሙያዎች። ‹‹የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያዎች ያረጁ እና መሸከም ከሚችሉት በላይ በመሥራት ላይ ያሉ ናቸው። የኤሌክትሪክ ፍላጎት ቢያድግም ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት እየተጠገኑ አይደለም›› ይላሉ የኢነርጂ ባለሙያው ጥጋቡ አታሎ።

የመንግሥት አማካሪው ሕዝቅያስ በዚህ ይስማማል። ‹‹በመሠረቱ የኃይል እጥረት እና መቆራረጥ የተከሰተው በኤሌክትሪክ እጥረት ሳይሆን እንደውም በዋነኝነት በጥገና ችግሮችም ጭምር ነው። በተለይም የማሰራጫ መስመሮች ከፍተኛ ኃይልን መሸከም ያለመቻላቸው እንዲሁም ከፍተኛ የደንበኞች ቁጥሮች ግን ከተወሰኑ መስመሮች የተገናኙ መሆናቸው ከአቅማቸው በላይ እንዲሠሩ አድርጓቸዋል›› ሲሉ ሕዝቅያስ ያነሳሉ።

ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ የ58 ንዑስ ማሰራጫዎች ግንባታ እና የ1,395 ኪሎ ሜትር የ132 ኪሎ ቮልት እና 522 ኪ.ሜ የ 230 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያዎች ግንባታና ማሻሻያ ተጠናቅቋል። ከዚህ ባሻገር እንደ ሕዝቅያስ ገለፃ፣ የኤሌክትሪክ አቅርቦት አስተማማኝነት ለመጨመር የኤሌክትሪክ ኃይል ብክነትን ለመቀነስ እንዲሁም ተጨማሪ አዳዲስ ንግዶችንና አባወራዎችን አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ አሁን ያሉትን ማሰራጫዎች ለማሻሻል መንግሥት አቅዷል።

‹‹በአሁን ሰዓት በአዲስ አበባ፣ አዳማ እና ሐዋሳ ጨምሮ በስድስት ዋና ዋና ከተሞች የማሰራጫ ጣቢያዎችን እንዲሁም ማስተላለፊያዎችን በማሻሻል ላይ ነን።›› ብለዋል ሕዝቅያስ።
በተግባር ላይ እየዋሉ ያሉት ማሻሻያዎች ይበል የሚያሰኙ ቢሆንም መንግሥት እየሄደበት ካለበት ፍጥነት አኳያ ችግሩን ለመፍታት ብዙ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ባለሙያዎች ያነሳሉ። ‹‹መንግሥት በበጀት እጥረት እና በችሎታ ክፍተት የተነሳ ማሻሻያዎችን በመላው አገሪቷ ለማከናወን ጊዜ ሊወስድበት ይችላል›› ብለው የሚያስቡት ጥጋቡ፣ ለአብነትም ትራንስፎርመር ግዢ ላይ ያለውን ችግር ያነሳሉ።

ምንም እንኳን ትራንስፎርመር በአገር ውስጥ ለማምረት የተደረገው ሙከራ የሚበረታታ ቢሆንም የሚሉት ጥጋቡ፣ ከፍላጎት አኳያ የሚመረተውም ሆነ ከውጭ የሚገባው አነስተኛ ነው ይላሉ። በተጨማሪ የትራንስፎርመሮች ግዢ የሚወስደው ሂደት ረጅም እና በፌዴራል መንግሥት ብቻ የሚከናወን መሆኑ ችግሩን አባብሶታል በማለት ያክላሉ።

ታዲያ እነዚህ ችግሮች የተረዱት የዓለም ዐቀፍ የግል ኢንተርፕራይዞች ማእከል የምሥራቅ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር ኃይለመለኮት አስፋው፣ ንዑስ ማሰራጫዎችን እና ማስተላለፊያዎችን የመገንባት፣ የማደስ እንዲሁም የመቆጣጠር ሥራ ለግሉ ዘርፍ ቢተው ችግሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍታት እንደሚቻል ያነሳሉ።

መንግሥት ግን ለጊዜው ይህንን ሥራ በራሱ ኃይል እና ከዓለም ዐቀፍ አበዳሪዎች እንዲሁም በራሱ በጀት ለመተግበር ያሰበ ሲሆን፣ ነገር ግን የኤሌክትሪክ ማመንጨት ሥራዎችን ከግሉ ዘርፍ ጋር በአጋርነት ለመሥራት አቅዷል።

‹‹ከአሁን በኋላ አዳዲስ የኃይል ፕሮጀክቶችን አንጀምርም። ትኩረታችንን በግንባታ ላይ ያሉት የንፋስ ማመንጫ ፕሮጅቶችን እንዲሁም ግድቦችን በማጠናቀቅ ላይ ይሆናል። እነዚህን ፕሮጀክቶች ከጨረስን በኋላ የማሰራጨት ሥርዓቱን እና ንዑስ ንዑስ ፕሮግራሞችን የማሻሻል እና ዘመናዊ የማድረግ ሥራዎች ላይ ብቻ እናተኩራለን›› ሲሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ሞገስ መኮንን አንስተዋል።

ይሁን እንጂ ኃይለመለኮት መንግሥት ብዙ ከተሞችን ሊያበራ የሚችል ኤሌክትሪክ ብክነት ማሰራጫዎች ድክመት ጋር በተያያዘ መከሰቱን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የግሉ ዘርፍ በዚህ ላይ እንዲሳተፍ የፖሊሲ ለውጥ ማድረግ እንደሚገባው ያነሳል። ይህም በኃይል እጦት የተነሳ የቆሙ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ እንዲሁም በሥራ ላይ ያሉት ኢንዱስትሪዎች ምርታማነትን በመጨመር የበለጠ የውጭ ምንዛሬ ለአገሪቷ ማስገኘት ይቻላል ይላሉ፣ ኃይለመለኮት።

በተጨማሪ ኤሌክትሪክ የማስተላለፍ ሥራ ለግል ዘርፉ ከተሰጠ ብዙ ድርጅቶች ወደ ሥራ ሊገቡ የሚችሉበት አጋጣሚ ይፈጠራል የሚሉት ኃይለመለኮት፣ ይህም በፍጥነት የጥገና ሥራዎችን ከማከናወን አኳያ አዎንታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል ሲሉ ምክራቸውን አጋርተዋል። የመንግሥት ሥራ መቆጣጠር እና ታሪፍ ማውጣት ብቻ ሊሆን ይገባል ሲሉም አክለዋል።

ነገር ግን የኢነርጂ ባለሙያው ጥጋቡ መንግሥት የታሪፍ ማሻሻያ ካላደረገ የግል ድርጅቶች በኤሌክትሪክ ማመንጨት ሥራ ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ላያሳዩ ይችላሉ ሲሉ ያነሳሉ። ‹‹መንግሥት የግሉ ዘርፍ የኢነርጂ ዘርፍ ላይ በሰፊው መዋዕለ ንዋይ እንዲያፈስ ለማድረግ የታሪፍ ማሻሻያ ማድረግ ይገባዋል›› ሲሉ ጥጋቡ ያነሳሉ። መንግሥትም ይህንን በመረዳት ታሪፍ ማሻሻያዎችን ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ሕዝቅያስ አውስተዋል።

በሌላ በኩል የኃይል እጥረት ችግርን ለረጅም ጊዜ ለመፍታት ግድቦችን በመገንባት ላይ የተሰጠው ትኩረትን በመቀነስ ሌሎች የኃይል ምንጮች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ባለሙያዎች ያነሳሉ። በተለይም በከተሞች የሚገነቡ ሕንፃዎች የራሳቸውን ኃይል ከፀሐይ ማመንጨት እንዲችሉ ማድረግ እንደሚገባ የሚያነሱት ኃይለመለኮት፣ መንግሥት ሌሎች የኢነርጂ አማራጮችንም ሊያይ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 86 ሠኔ 20 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here