በኢትዮጵያ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚረዱ በሰዓት ከአንድ ሺሕ ኹለት መቶ እስከ አንድ ሺሕ ስድስት መቶ ሃምሳ ዶላር የሚከፈልባቸው ኹለት አውሮፕላኖች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ተገለጸ።
የገቡት አውሮፕላኖች ኹለት ዓይነት ሲሆኑ፣ አንዱ በሰዓት 1200 የሚከፈልበት ሲሆን ሌላው ደግሞ 1650 የአሜሪካ ዶላር ወጪ ይደረግበታል። ረጅም ርቀት የሚበርሩ እና ብዙ ፀረ-ተባይ ኬሚካሎችን ተሸክመው መሄድ የሚችሉ ከሦስት እስከ አራት ቦታዎችን ረጭተው የሚመለሱ አውሮፕላኖች፣ አንድ ሺሕ ስድስት መቶ ሃምሳ ዶላር እንደሚከፈልባቸው ሲሆን፣ ከተጠቀሱት አነስ የሚል አገልግሎት የሚሰጡት ደግሞ 1200 ዶላር በሰዓት እንደሚከፈልባቸው የግብርና ሚኒስቴር የእፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር ዘብዲዮስ ፈላቶ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
እንደ ዘብዲዮስ ገለፃ አውሮፕላኖቹ ይግቡ እንጂ የአከፋፈሉ ሁኔታ ግን በሂደት ላይ ነው። የክፍያ ሁኔታቸውም በሰዓት የሚታሰብ እና የኹሉም አውሮፕላኖች ኪራይ ክፍያ እንደየሥራቸው እና እንደየመጠናቸው እንደሚለያይ ተናግረዋል። አክለውም የአውሮፕላኖቹ መግባት እና መጨመር ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ከዛም በተጨማሪ አሁን በሥራ ላይ ያሉ አውሮፕላኖች ስድስት ሲሆኑ አንደኛው በመታደስ ላይ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
በተያያዘ በኮቪድ 19 ኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሥራ ያቋረጠ አውሮፕላን እንደሌለ ቢገልፁም፣ ተፅዕኖው ግን ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ጠቅሰዋል። ከዚህ በፊት ኅብረተሰቡን ማዝመት እና የተወሰነ ቦታ በኅብረተሰቡ እንዲሸፈን የሚደረግበት ሁኔታ ነበር የሚሉት ዘብዲዮስ፣ አሁን ግን በኮሮና ምክንያት ያንን ማድረግ እንዳልተቻለ እና የአውሮፕላኖቹን ብቻ ውጤት መጠበቅ አመርቂ አይደለም ብለዋል።
ከዛም በተጨማሪ በመርጫ መሣሪያዎችም የሰው ኃይል ተጠቅመን ግዜም ቢወስድ እናቃልል ነበር። ነገር ግን አሁን ያንን ማድረግ አልተቻለም ሲሉ ዘብዲዮስ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
እንደሚታወቀውና አዲስ ማለዳ ደጋግማ በተለያዩ እትሞች ላይ እንዳወጣችው፣ የአንበጣ መንጋ ከጅቡቲ የሚገቡት በድሬዳዋ፣ በኬንያ በኩል የሚገባው ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ አርባ ምንጭ እና በኬልከሌ አካባቢ እየገባ መሆኑን እና የአንበጣ መንጋው ከሶማሊያ በአምስት አቅጣጫ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ ሸሽቶ የነበረው ዳግም ወደ ኢትዮጵያ እየተመለሰ ነው። ይህም ስጋቱን የበለጠ እንደጨመረውና በቀጣይም ለአንበጣ መንጋው መዛመት ምቹ የአየር ንብረት የሚያገኝ መሆኑ በተደጋጋሚ በተለያዩ ተቋማት የችግሩ አስከፊነት ሲገለፅ መቆየቱ የሚታወስ ነው።
በጣም አነስተኛ የሚባለው የበረሃ አንበጣ መንጋ እስከ ዐሥር ኪሎ ሜትር ሊረዝም እንደሚችል ዓለም ዐቀፉ የምግብ እና የግብርና ድርጅት መረጃ ያሳያል። አንድ የበርሃ አንበጣ በየቀኑ ከኹለት ግራም በላይ ወይም የራሱን ክብደት ያህል ምግብ የሚወስድ ሲሆን፣ በመንጋ ሲሆኑ በቀን 35 ሺሕ ሰዎች ሊመገቡት የሚችሉትን ያህል የመመገብ አቅም እንዳለው ተቋሙ ገልፆ ነበር።
በአንድ ሳምንት ውስጥ ሦስት ጊዜ እንቁላል የመጣል አቅም ያለው አንበጣው፣ በአንዴ ከ80 እስከ 120 እንቁላሎችን ከመፈልፈሉም ባሻገር አዳዲሶቹ አንበጣዎችም ከትልልቆቹ አንበጣዎች በብዙ እጥፍ የበለጠ ምግብ እንደሚመገቡ የምግብ እና የግብርና ድርጅት ባወጣው መረጃ አሳውቆ ነበር።
ቅጽ 2 ቁጥር 88 ሐምሌ 4 2012



