እስከ 10 ሺሕ የሚጠጋ ሰው ቫይረሱ ሊገኝበት እንደሚችልም ተጠብቋል
በኢትዮጵያ በአገር አቀፍ ደረጃ ከነሐሴ 1/2012 ጀምሮ በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ቀናት ውስጥ 200 ሺሕ ለሚደርሱ ሰዎች የኮቪድ 19 ምርመራ ለማድረግ እንደታቀደ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በዚሁ በአገር ዐቀፍ ደረጃ በሚጀመረው እንቅስቃሴም 80 ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎች በኹለት ሳምንት ውስጥ የሙቀት ልየታ እንደሚደረግ የጤና ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
በዚህ በኹለት ሳምንት በሚደረገው ንቅናቄ ውስጥ እስከ ዐስር ሺሕ የሚጠጋ ሰው በምርመራው የኮቪድ 19 ቫይረስ ሊገኝበት እንደሚችልም በእቅድ ደረጃም እንደተያዘ ተጠቅሷል። የምርመራ ሁኔታውም በየክልሉ እና በሁሉም ወረዳዎች እንደሚደረግ የጤና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዮርዳኖስ አለባቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
እንደ ዮርዳኖስ ገለፃ አገር ዐቀፍ ንቅናቄው ያስፈለገበት ምክንያት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጠረ ያለውን መዘናጋት ተከትሎ እየመጣ ያለውን የስርጭቱን መጨመር ለመቆጣጠር፣ ከመመርመር ባሻገር ደግሞ ማስተማር እና ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ነው ብለዋል።
ከዛም ባሻገር በምርመራው የተለዩትን ተጠቂዎች ከዚህ ቀደም በወጣው መመርያ መሰረት በከባድ ሁኔታ ቫይረሱ እየጎዳቸው ያሉትን ማለትም ፅኑ ታማሚ የሆኑትን አፋጣኝ ሕክምና እንዲሰጣቸው ማድረግ ነው። የተቀሩትን እና የቫይረሱ ተፅእኖ ያልጎላባቸው እንዲሁም ምልክት የማያሳዩትን ደግሞ ቫይረሱ እንዳለባቸው በማመላከት እራሳቸውን አግልለው እንክብካቤ እንዲያደርጉ መጠቆም ነው ብለዋል።
ከዛም ባለፈ ግን የቫይረሱን ስርጭት በምን ያህል ደረጃ እንደሆነ ለማየት እና የአቅጣጫ ለውጥ ማድረግ ካስፈለገ እሱን ለመቀየስ እንደሚያስችል ታስቦም ነው ሲሉ ዮርዳኖስ አለባቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የማኅበረሰብ ዐቀፍ ንቅናቄ እና ምርመራ መጠናከር እንዳለበት እና የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተጠናከረ ማኅበረሰብ ዐቀፍ ንቅናቄ እና ምርመራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ደመቀ መኮንን ገልፀው ነበር። የሚኒስትሮች ኮሚቴ በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ወቅታዊ ሁኔታ እና ቀጣይ አዝማሚያ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም እንዲሁም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ተወያይተው እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።
ሐምሌ 9/2012 ላይ በተደረገው በዚህ ውይይት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ የጤና ሚኒስቴር አማካሪ ዶክተር ስንታየው ፀጋዬ ጥናታቂ ጽሑፍ አቅርበው ነበር። በዛም የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ከተከሰተ ከመጋቢት ወር ጀምሮ እስከ ሐምሌ ወር ያለውን የስርጭት ሁኔታ የተመላከተበት ነው።
ባለሞያው እንዳመላከቱት ከሆነ በወረርሽኙ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፆታ አንፃር 61 በመቶ ወንዶች 39 በመቶው ደግሞ ሴቶች ናቸው። በበሽታው ከተያዙ ሰዎች 92 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ምንም አይነት ምልክት እንደማያሳዩ በዳሰሳ ጥናታቸው አመላክተዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፣ የመከላከል ሥራ ላይ በይበልጥ መሥራት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የተጠናከረ ማኅበረሰብ ዐቀፍ ዘመቻ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህ ደግሞ ወረርሽኙን በመግታት ስኬት ካገኙ አገራት ልምድ ከመውስድ ባለፈ የእነርሱን መንገድ በመከተል ጠንካራ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ አጽንዖት ሰጥተዋል።
የመከላከል ዘመቻውንም አገራዊ አጀንዳ በማድረግ እያንዳንዱ ዜጋ እንዲተገብር የተጠናከረ ማኅበረሰብ ዐቀፍ ንቅናቄ እና ምርመራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው እንደነበርም ይታወሳል።
ቅጽ 2 ቁጥር 92 ነሐሴ 2 2012



