ከሰሞኑ በመኪና የሚደረጉ ስርቆቶች መብዛታቸውን በብዛት እየሰማን ነው። በተለይም ከኮሮና ቫይረስ መከሰት በኋላ በሰዎች መካከል ርቀትን ለመጠበቅ በሚል የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሸከርካሪዎች የሚጭኑት ሰው ቁጥር መጠን በግማሽ ቀንሷል። ይህም ለዘራፊዎችና ለሌቦች የበለጠ ምቹ አማራጭ የፈጠረ ይመስላል።
ታድያ ብዙዎቹ ተሸወድን የሚሉ ሰዎች የሚናገሯቸው ክስተቶችና የአሰራረቅ ሁኔታው እንዳለ ሆነው የ‹ሴቶች› ሥም ይነሳል። ‹ጋቢና የተቀመጠችው ሴት ነበረች› ወይም ‹ከተሳፋሪዎች መካከል ሴቶችም ነበሩ› ሲሉም ይሰማል። ይህ ማለት ሴት በዘረፋ ላይ ትብብር ታደርጋለች ብለን አናምንም የሚል ሐሳብ ያዘለ ነው።
ነገሩ ቀልድ ሊመስል ወይም ለብዙዎች ላይዋጥላቸው ይችላል። ምን መሰላችሁ! እነዚህ ሌቦች በተሻለ የማኅበረሰቡን አስተሳሰብ የተረዱት ይመስለኛል። በማኅበረሰባችን ሴቶች ሊሰርቁ አይችሉም የሚል አመለካከት አለ። አይችሉም ስል አቅም የላቸውም ማለት ወይም ‹በሌብነት ሴቶችን እናብቃ› የሚል ቀልድ ለመቀለድ አይደለም።
ነገር ግን ሴቶች በጸባያቸው ሩህሩህ፣ የሰው ንብረት ሊነኩ የማይወዱ፣ ስርቆትን የሚጠየፉና ሲሆን የሚኮንኑ ናቸው ተብሎ ይታመናል። በአንጻሩ በእርግጥ ሴቶች ገንዘብ ወዳድና ካለው የሚጠጉ ተደርገው መሳላቸውም የምንረሳው አይደለም። ነገሩ ትንሽ የሚጣረስ ይመስላል።
ብቻ ግን ሴቶች የተሳፈሩበት ስለሆነና ሴቶች በሌብነት ስለማይሳተፉ በሚል በ‹ሿሿ› መዘረፋቸውን የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው። ይህ ታድያ በአጠቃላይ ያለብንን ችግር ያሳያል፤ ጠቅልለን የመደምደም አመል አለብን።
ፀጉሩን ያንጨባረረ፣ አለባበሱ ግዴለሽ የሆነ ሰው ሁሉ ሌባና ዱርዬ ይመስለናል። ወይም ሌባና ዱርዬ እንደሆነ እናምናለን። እናም ከዚህ ዓይነት ሰው ስንጠነቀቅ ሱፍ የለበሰ፣ ፀጉሩን በስርዓት የተስተካከለ፣ ሳምሶናይት የያዘና የተረጋጋ ሰው ከአጠገባችን ሆኖ ሰርቆን ይሄዳል።
በእርግጥ እነዚህ ነገሮች በማኅበራዊ ትስስራችን መካከል መተማመንን የሚሸረሽሩ መሆናቸው ግልጽ ነው። ‹ማንን ነው የማምነው?› ያሰኛል። ሌላው ቀርቶ በቁጣ ይመለሳሉ የሚባሉ ሕጻናትን ሳይቀር በሌብነት አሰማርተው ልጆችን እንኳ ለማመን ሁኔታው ከባድ እየሆነ እንደሆነ ማስተዋል እንችላለን።
ሌቦች በየጊዜው የሚጠቀሙት ስልት እያደገና እየሰፋ ተማምነን የተውናቸውን ጉዳዮች እየመዘበረ ይገኛል። ይህ ግን ምንአልባት ጠቅልሎ የመደምደም ባህላችንን ሊቀይር ይችላል የሚል እምነት አለኝ። በአለባበስ፣ በጾታ፣ በብሔር፣ በሥራ ሁኔታ፣ በአነጋገር ወዘተ ደምድመን ‹እንዲህ ከሆነ እንዲህ ነው› ብለን የዘጋናቸውን ጉዳዮች መልሶ ያስከፍተናል።
‹አለባበሱ ቢያምርም ማንነቱ እንደዛ ላይሆን ይችላል፣ ሴትም ብትሆን ልትሰርቅ ትችላለች፣ ስለተንጨባረረ ብቻ ሌባ ላይሆን ይችላል› ወዘተ ብለን ማሰላሰል ይኖርብናል። እንዳልኩት ነው፤ ይህ ማኅበራዊ ትስስራችን ላይ፣ መሥርተን የቆየነው መተማመን ላይ ጥላሸት ይጥላል። ሆኖም ግን በሚገባው ቦታ ሁሉ ጥርጣሬ ሊኖር ይገባል።
ጊዜ ብዙ ነገሮችን ይለውጣል። አሁን አንድ ሰው በራሱ እንጂ በማንም በሌላ እርግጠኛ መሆን የሚችልበት ጊዜ እንዳይደለ መረዳት ላይ ደርሰናል። ስለሴቶች ስናወራ ሁሉም ሴቶች አንልም፣ ስለወንዶች ስናወራ ሁሉም ወንዶች አንልም። ስለብሔርም ከተነሳ ሁሉም የዚህና የዚያ አካባቢ ተወላጅ ብሎ መደምደም አይቻልም። ይህን በሿሿ ውስጥ መረዳት የሚቻል ይመስለኛል።
እንተማመን፣ ግን ሁላችን እያንዳንዳችን ለቃላችን፣ ለቦታችን፣ ለኃላፊነትና ሥልጣናችን፣ ለራሳችንና ለአገራችን እንታመን። ‹ሰው አይታመንም› ስንል፣ እኛም ሰው ነንና ሌላ ፍጡራን የምንለውን ቢሰሙ ‹ሰው አይታመንም› ያልነውን ተናጋሪዎችም አያምኑንም። በሿሿ የማንዘረፈው ያንን መተማመን መልሰን ስናገኝ ይመስለኛል ለማለት ነው።
ሊድያ ተስፋዬ
ቅጽ 2 ቁጥር 93 ነሐሴ 9 2012


