ተከሳሾች ለተጨማሪ ክርክር ይቀርባሉ
በዎላይታ ዞን የተፈጠረውን አለመረጋጋት በተመለከተ ከአካባቢው ህዝብ ጋር ለመመምከር ከደቡብ ክልልና ከፌደራል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ቡድን ወደ ሶዶ ከተማ ያቀኑ የዞኑ ተወላጆች በወንጀል ተጠርጥረው የተከሰሱ የዞኑ አመራሮች ክሳቸው እንዲቋረጥ ለጠቅላይ ሚኒስቴሩ እናቀርባለን ማለታቸው ተስማ።
የተጠርጣሪ አመራሮቹ ክስ እንዲቋረጥ ለጠቅላይ ሚነስቴር ጥያቄ ይቀርባል የተባለው የዞኑ “ከፍተኛ አመራሮች ክሳቸው ካልተቋረጠ ሌሎች በዞኑ የሚታዩ ችግሮችን መፍታት አይቻልም” በሚል በሶዶ ከተማ በነበረው ውይይት ላይ የተሳተፉ የዞኑ መምሪያ ኃላፊዎችና ሌሎች ተሳታፊ አካላት ባነሱት ጥያቄ መሰረት መሆኑን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ጠቁመዋል።
ከሳምንታት በፊት በዞኑ ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት እጃቸው አለበት ተብለው በመጠርጠራቸው በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪን ጨምሮ ሌሎች 20 ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ነው። ቢሆንም የአካባቢው ማህበረሰብ የአመራሮቹ ጥያቄ የዞኑ ህዝብ ሙሉ ጥያቄ እንጅ የግለሰብ ጉዳይ አይደለም ስለሆነም አመራሮቹ ይለቀቁልን፣ የተከሰሱ አመራሮች ወንጀለኛ ከሆኑ እኛም ወንጀለኞች ነን የሚል ሀሳብ እያስተጋቡ መሆኑን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ምንጮች ጠቁመዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት በዎላይታ ሶዶ ከተማ ከዞኑ መምሪያ ኃላፊዎችና ከሌሎች የወረዳ አመራሮች ጋር በተደረገው ወይይት በዞኑ ያለው የንግድ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ እየተንቀሳቀሰ ባለመሆኑ ለችግሩ አስቸኳይ መፍትሔ እንደሚሻው ከፌደራልና ከክልል ለተላኩ አመራሮች ጋር የተወያዩ አካላት አሳስበዋለ ተብሏል።
በተጨማሪም በጽሑፍ ደብዳቤ የተደገፈ መረጃ ለአዲስ ማለዳ የደረሱ ጥቆማዎች እንደሚሳዩት በዞኑ ስሞኑን መንግስት በተሳሳተ መንገድ በዎላይታ ህዝብ ላይ እያደረሰ ነው ያሉትን እርምጃ በመቃወም እንዲሁም መንግስት ችግሩን በአስቸኳይ እንዲፈታ የተሰጠውን ዕድል በአግባቡ አልተጠቀመም በማለት በዎላይታ ዞን ውስጥ በተለያዩ መንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ በስራ ላይ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች ችግሩ በአግባቡ እስኪፈታ ድረስ ከብልፅግና ፓርቲ ለጊዜው ራሳቸውን ማግለላቸውን በፊርማቸው በማረጋገጥ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡
በአንፃሩ በዎላይታ ዞኑ ተፈጥሮ የነበረውን ወቅታዊ ችግር ለማስተካከል በሚል ከፌዴራልና ከክልል ወደ ሶዶ ከተማ ያቀኑ የዎላይታ ተወላጅ ከፍተኛ አመራሮች በተናጠል ነጋዴዎችንና ወጣቶችን ለማወያየት ጥሪ ቢደርጉም አለመሳካቱን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአዲስ ማለዳ ምንጭ አስረድተዋል።
እንደ አዲስ ማለዳ ምንጭ ገለፃ የውይይቱ ሀሳብ የቀረበው በወቅታዊ ጉዳይ ውይይት ለማድረግና የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግሮችን በጋራ እንዲፈታ ለማወያየት ያለመ እንደነበር ጠቁመዋል። ነገር ግን ማህበረሰቡ በአመራሮቹ እስር ምክንያት በአወያዮች ላይ ችግር ይፈታሉ የሚል እምነት የአካባቢው ማህበረሰብ እንደሌለው የአዲስ ማለዳ ምንጭ አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወላይታ ዞን አመራሮችን ጨምሮ ለ20 ተጠርጣሪዎች በተፈቀደው ዋስትና ላይ ፖሊስ ያቀረበውን ይግባኝ ለመመልከት ለሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ፍርድ ቤቱ ባለፈው ረቡዕ ነሐሴ 20/2012 በሐዋሳ ከተማ ባስቻለው ችሎት ተጠርጣሪዎቹ ሳይቀርቡ በመቅረታቸው ሌላ ቀጠሮ መስጠቱን ተገልጿል።
ፍርድ ቤቱ ባዋለው የችሎት ሂደት ተጠርጣሪ ተከሳሾች ባይቀርቡም በጠበቆቻቸው በኩል የክርክር ሂደት መካሄዱ ተገልጿል። በችሎቱ አቃቤ ህግ ለተጨማሪ ክርክር ተጠርጣሪ ተከሳሾች ተይዘው ለነሀሴ 27/12/12 እንድቀርቡ ተወስኗል። በዞኑ ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር ከ16 በላይ ሰዎች ሂወታቸውን ማጣታቸው የሚታወስ ነው።
ቅጽ 2 ቁጥር 95 ነሐሴ 23 2012



