የኢትዮ- ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ተደጋጋሚ የስርቆት ወንጀሎች እየተፈፀሙበት እንደሚገኝ ተጠቆመ።
የኢትዮ – ኬንያ የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ኮንቨርተር ጣቢያ ፕሮጀክት የግንባታ አስተባባሪ ሰይፉ ፈይሳ እንደገለፁት በኢትዮጵያ በኩል የሚገነባው የ433 ኪሎ ሜትር የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል ብለዋል፡፡
ይሁን እንጅ በወላይታ ዞን አንዳንድ አካባቢዎች በማስተላለፊያ መስመሩ ሽቦዎች እና የምሰሶ ብረቶች ላይ በተደጋጋሚ የስርቆት ወንጀሎች እየተፈፀመበት ሲሆን ይህም ተቋሙን ለተጨማሪ ወጪ በመዳረግ ከ34 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራም እንዳደረሰበት አስታውቀዋል፡፡
ኪሳራው የደረሰው በስርቆቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰበትን የማስተላለፊያ መስመሩን አካላት በአዲስ ለመተካትና ለመቀየር፣ እንዲሁም ለመበየድ፣ ለዕቃ ግዥ እና ለምሶሶ (Tower) ቅየራ ተጨማሪ ወጪ በመውጣቱ ነው ተብሏል፡፡
የማስተላለፊያ መስመሩ 994 ምሶሶች ያሉት ሲሆን በተፈፀመው ስርቆት ጉዳት ከደረሰባቸው ምሶሶዎች መካከል አንዱን ሙሉ በሙሉ መቀየሩን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡
የግንባታ ሰራው በ2008 የተጀመረው የኢትዮ- ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ከ185 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በጀት ተይዞለት በመከናወን ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጰያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዘገባ አመላክቷል።



