የሚዲያ ተቋማትን ከሳይበር ጥቃት መከላከል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ለመስራት የኢትዮጵያ ብሮድካሰት ባለስልጣን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በጋራ ለመስራት ተስማሙ።
ስምምነቱ የሚዲያ ተቋማትን ከማንኛውም የሳይበር ጥቃት በመከላከል አስተማማኝና ደህንነታቸው የተረጋገጠ የሚዲያ ተቋማት መገንባትን ያለመ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ግዛው ( ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ባለፈው 2012 በጀት አመት በሀገራችን የሳይበር ጥቃት ከተሰነዘረባቸው ዘርፎች፤ ከፋይናንስ ተቋማት በመቀጠል የሚዲያ ዘርፉ በ2ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ሹመቴ ጠቁመዋል፡፡
በሚዲያ ተቋማት ላይ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶች እያደጉ መምጣታቸዉ መረጃ የዘመናችን ቁልፍ ሃብት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚከሰት እንደሆኑ ያነሱት የኤጀንሲዉ ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ይህም የመገናኛ ብዙሃን ለመረጃ መንታፊዎች በቀዳሚነት ዒላማ መሆናቸውን ያሳየ ነዉ ብለዋል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ ኃላፊነት ይውሰድ እንጂ የሳይበር ደህንነት ጉዳይ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ተቋማት ትኩረት የሚያሻው መሆኑን ሹመቴ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር) በበኩላቸው የዘመኑ ዉጊያ እንደቀድሞዉ ፊት ለፊት የሚከወን ሳይሆን የበላይነት ለማረጋገጥ የሚደገው እሽቅድድም በመረጃ እና ከመረጃ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ነው ብለዋል፡፡
መገናኛ ብዙሃን መረጃን በትክክል ለአድማጭ ተመልካች የማድረስ ሃላፊነት እንዳለባቸው የጠቀሱት ዶ/ር ጌታቸዉ ለዚህም መረጃዎቹ ከሳይበር ጥቃት ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ መዘዋወር እንደሚገባቸዉ ገልጸዋል፡፡
የመገናኛ ብዙሃን ባህሪን መሰረት ያደረገ ድጋፍና ክትትል ማድረግ፤ ደህንነቱ የተጠበቀ የቴክኖሎጂ መሰረተ-ልማት ዝርጋታ፣ ሚዲያ ክትትል ሂደቱን የማዘመን (Automation) ፣ የሳይበር ደህንነት ምርመራ እና መሰል ጉዳዮች ላይ ባለስልጣኑ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በቀጣይ በጋራ የሚሰሩባቸው ጉዳዮች ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።



