በዳጉ ሚድያ፣ ፌስቲቫልና አዋርድ የተዘጋጀ ትኩረቱን የዓለም አእምሮ ጤና ቀን ላይ መሠረት ያደረገ መድረክ የፊታችን ቅዳሜ መስከረም 30/2013 ማምሻውን ከ11 ሰዓት ጀምሮ ቦሌ በሚገኘው ሞዛይክ ሆቴል ተዘጋጅቷል።
በዚህ መሰናዶ ከአማኑኤል ሆስፒታል የሚመጡ የአእምሮ ጤና ሐኪሞች ይገኛሉ ተብሏል።
ከአእምሮ ጤና ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ስላለው የግንዛቤ መጠንና ነባራዊ ኹነቶችን የሚነሱ ሲሆን፣ ከመገናኛ ብዙኀን ምን ይጠበቃል በሚለው ላይም ሐሳባቸውን እንደሚያቀርቡ ተገልጿል።
በመድረኩም ከአእምሮ ሕመም የዳኑ ሰዎች ልምዳቸውን እንደሚያጋሩ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ማናዬ እውነቱ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።
የዳጉ ሚድያ ፌቲቫልና አዋርድ ዋና አዘጋጅ የሆነው ዳጉ ኮሚንኬሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር የአእምሮ ጤና ላይ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በሚመለከት በጋራ ሲሠራ ቆይቷል።
በተመሳሳይ በተለያዩ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ጋዜጠኞችና የሚመለከታቸው ባለሞያዎች የሚገናኙበትን ወርሃዊ መድረክ የሚያዘጋጅ ነው።



