የቤተ አባይ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ማዕከል ግንባታ አልተጀመረም

በባህርዳር ከተማ በተለምዶ አባይ ማዶ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ወደ ቤዛዊት ማርያም በሚወስደው መንገድ በአማራ ክልል ዲያስፖራ ማህበረሰብ እና በክልሉ ምሁራን ድጋፍ ሊገነባ ታቅዶ የነበረው የቤተ አባይ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ማዕከል ግንባታ አለመጀመሩ ተገለጸ።

በ2008 የመሠረት ድንጋይ ቢቀመጥም ምንም አይነት ግንባታ ሳይጀመር ዓመታት ተቆጥረዋል። ‹‹ከአራት አመታት በፊት የመሰረት ድንጋዩ የተቀመጠው ቤተ አባይ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ማዕከል ምንም አይነት ግንባታ ሳይጀመር ቆሞ ቀርቷል ›› ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የመሠረት ድንጋዩ በተቀመጠበት ወቅት የዲያስፖራ ኮሚቴ እና የአማራ ምሁራን ማህበር አባል የነበሩ ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ ግለሰብ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት በወቅቱ ከክልሉ መንግስት በነፃ የተበረከተላቸው አምስት ሽሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚታነፅ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አዳሪ ትምህርት ቤት ጭምር የያዘ የኢኖቬሽን ማዕከል ሊገነቡ እንደነበረ አስታውሰው በአማራ ክልል ዲያስፖራ አባላት ለቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ማዕከሉ ግንባታ የቴክኖሎጂ እና ሙያዊ የሆነ እገዛ እንደሚያደርጉ እንጂ ሙሉ በሙሉ የገንዘብ ድጋፉን ለማድረግ ቃል እንዳልገቡ ተናግረዋል። አያይዘውም የሳይንስ ማዕከሉ ቢገነባ ለአካባቢው ተወላጅ ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን በክልሉ ለሚገኙ ከዚያም ከፍ ሲል ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ለሚመጡ ተማሪዎች ጥቅም ላይ ሊውል ይችል እንደነበር ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የቤተ አባይ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ማዕከል መገንባት አገሪቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር ለምታደርገው ጉዞ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ተናግረው ‹‹አሁንም ቢሆን ግንባታው እውን እንዲሆን ግንባታውን ማንም ያስገንባው ማንም›› የበኩላቸውን ከማበርከት ወደኋላ እንደማይሉ አስረድተዋል። በወቅቱ ለግንባታው የሚሆን አምስት ሽሕ ካሬ ሜትር ቦታ ከክልሉ መንግስት በነጻ እንደተበረከተም አዲስ ማለዳ ከዚህ ግለሰብ ተረድታለች። የግንባታው የመሰረት ድንጋይ በተቀመጠበት ወቅት ሀምሌ አንድ 2008 የአማራ ክልል መገናኛ ብዙሃን እና የኢትዮጲያ ፕሬስ ድርጅት የሰሩት ዜና ላይ የተገለፀው ግን ለግንባታው 20 ሸሕ ካሬ ሜትር እንደተሰጣቸው ነው።

የክልሉ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ መላኩ ጥላሁን በበኩላቸው ይህንን ግንባታው ያልተጀመረ ፕርጀክት በኃላፊነት ወስደው ለማሰራት በጀት ቢጠይቁም የክልሉ መንግስት የባለቤትነት የፈቃድ ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እስኪሰጣቸው እየተጠባበቁ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። ኃላፊው አክለውም በወቅቱ የመሰሠረት ድንጋዩ ሲቀመጥ ሕንፃውን ለማሠራት ኃላፊነቱን የወሰደው የአማራ ዲስፖራ ማህበር በክልሉ በተደረገው የአማራ ምሁራን ጉባኤ ላይ ነበር ሲሉ አስታውሰዋል።

የክልሉ መንግስት ለክልሉ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ሕንፃውን እንዲያስገነባ ኃላፊነት ከወሰደው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን የሕንፃውን ዲዛይን ለማሠራት እየተነጋገረ እና ካርታ እና ፕላኑን ለማሠራት እየሞከረ መሆኑን እና ቤተአባይ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ማዐከል የቴክኒሎጂ ፓርክ እንዲባል ማሰባቸውን ነው መላኩ ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት።

ግንባታው በክልሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ የሚገነባ ከሆነ በውስጡ የምርምር የፈጠራ የአመራርና አስተዳደር፣ የፓርክ አስተዳደር የገበያ ጥናት የሙያና ስልጠና እና የማህበረሰብ የጥናት ማዕከል በውስጡ ከሚይዛቸው መካከል ጥቂቶቹ ሲሆኑ ዲዛይኑ ሲሰራ ሊጨመሩ የሚችሉ ማስፋፊያዎች እና ተማሪዎች የተለየ ተሰጥኦአቸውን የሚያዳብሩበት የተለዩ የጥናትና የምርምር እና የማሳያ ቦታዎች እንደሚኖሩትም ነው መላኩ ያስታወቁት።

የግንባታው መሰረት ድንጋይ በተቀመጠበት ሐምሌ 2008 ላይ 500 ሚሊዮን ብር ለግንባታ ተመድቦ የነበረ ቢሆንም አሁን ባለው የግንባታ እቃወች ሒሳብ ደግሞ ለግንባታው የሚወጣው ወጪ እየተጠና እንደሆነ እና የቴክኖሎጂ ማዕከሉ ግንባታ በተቻለ መጠን በቅርቡ ግንባታው ሊጀመር እንደሚችል እና እርሳቸው በኃላፊነት የሚመሩት የክልሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ የበኩሉን ጥረት እያደረገ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

በክልሉ እንደዚህ ያለ ሰፊ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከል አለመኖሩን እና የዚህ ማዕከል መገንባት ትልቅ ስኬት እንደሚሆን ነው መላኩ ሃሳባቸውን የሰጡት።

ቅጽ 2 ቁጥር 104 ጥቅምት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here