የተሽከርካሪዎችን የበካይ ጋዝ ልቀት እና የነዳጅ ደረጃ ደገብ ሊጣልበት መሆኑን ተጠቆመ

0
1098

ኢትዮጵያ የምታስገባው ነዳጅ ከደረጃ በታች ነው

በኢትዮጵያ ከተሽከርካሪዎች ወደ አካባቢ አየር የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ በአየር ንብረት ብክለት ላይ ሚስከትለውን ጫና ለማስቀረት የተሸከርካሪዎችን የጋዝ ልቀት ደረጃ የሚወስን መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ አካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ።

በአዲስ አበባና እና ሌሎች ትላልቅ ከተሞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የተሽከርካሪዎች በካይ ጋዝ ልቀት ለመገደብ በረቂቅ ደረጃ እየተዘጋጀ ያለው የደረጃ መመሪያ በኹለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ደረጃ እንደሚያስቀምጥ የኢትዮጵያ አካባቢ፣ አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የአካባቢ ሕግ ተከባሪነትና ቁጥጥር ዳይሬክተር ግርማ ገመቹ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። እነዚህም ከተሽከርካሪ የሚለቀቅ በካይ ጭስ በደረጃ መገደብና የነዳጅ አይነቶችን ደረጃ ማውጣት የሚሉት መሆናቸወን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የምታስገባው ነዳጅ የጥራት ደረጃ ሲመዘን ከደረጃ በታች መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ከደረጃ በታች የሆነ ነዳጅን በሕግ ማገድ የመጀመሪያው ሥራ መሆን አለበት ብለዋል።

በኢትዮጵያ በትራፊክ ሕግ መሰረት አንድ ተሸከርካሪ እየተነዳ ጥቁር ጭስ ካወጣ በትራፊክ ሕግ እንደሚያስቀጣ ያስታወሱት ግርማ፣ ጥቁር ጭስ በትራፊክ ሕግ ቢያስቀጣም የበካይነት ደረጃ እስካሁን እንዳልወጣለት ገልጸዋል።

የነዳጅ ደረጃ ረቂቂ የተዘጋጀው በአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ መሰረት መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክውተሩ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አሮጌ ተሸከርካሪዎችን በእድሜ ገደባቸው እንዳይነዱና እና ከውጭ እንዳይገቡ ያወጣውን አዋጅ የሚደግፍ ነው ተብሏል። የተሸከርካሪዎች ነዳጅ እና የጋዝ ልቀት ደረጃ መወሰኑ አሮጌ መኪኖች በሂደት ከአገልግሎት እንዲወጡ እንደሚረዳ ተመላክቷል። በካይ ጥቁር ጭስ የሚፈጠረው ከመኪኖች ሞተር ማርጀት ጋር የተገናኘ መሆኑን የገለጹት ግርማ ከአሮጌ መኪኖች በሚወጣው ደረጃ በሂደት እንዲጠፉ ያደርጋል ብለዋል።

ከተሸከርካሪዎች የሚወጣው ጭስ የካርበን ልቀት ከተቀመጠው ደረጃ በላይ መሆን አለመሆኑን መለኪያ ማሽን በሚሰጠው መረጃ መሰረት የተቀመጠውን ደረጃ ተላልፈው ከተገኙ ወደፊት በትራፊክ ሕግ በሚወሰን ቅጣት እንደሚቀጡ ግርማ ለአዲስ ማለዳ አመላክተዋል። በረቂቅ ደረጃ የተዘጋጀውን የነዳጅ እና ጋዝ ልቀት ደረጃ ሀሳብ ያመጣው ኢትዮጵያ አካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ሲሆን በረቂቁ ዝግጅት ትራንስፖርት ሚኒስቴርም እንደ አንድ ባለድርሻ አካል መሳተፉን ግርማ ተናግረዋል።

የተሸከርካሪ ጭስ እና የነዳጅ ደረጃን ይገድባል የተባለው ደረጃ ምደባ መመሪያ በኢትዮጵያ ትራንስፖርት ባለስልጣን ረቂቁን እንዳዘጋጀው የጠቆሙት ግርማ ኮሚሽኑ በቴክኒክ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል። የደረጃ ምደባ ረቂቁ ተግባራዊ የሚሆነው በኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ተገምግሞ ከጸደቀ በኋላ መሆኑን ግርማ ጠቁመዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ ተሸከርካሪ ይበዛባቸዋል ተብለው በተለዩ ቦታዎች ላይ ከተሸከርካሪዎች የሚወጡ ጭሶች ምክንያት የአየር ብክለት መጠን የዓለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው መስፈርት በላይ መሆኑን አዲስ ማለዳ በ95ኛ እትሟ መዘገቧ ይታወሳል።

በአፍሪካ የአሮጌ ተሸከርካሪዎች ሽያጭ ብክለትን እያስከተለ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባውጣው ሪፖርት አስታውቋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሮጌ ተሽከርካሪዎች ከሀብታም አገራት እየወጡ በድሃዎቹ የአፍሪካ አገራት ማራገፊያ ሆነዋል ሲል ተመድ በሪፖርቲ አስፍሯል።

የአካባቢ ጥበቃ ባለሞያዎች ወደ አፍሪካ አገራት ከሚላኩ ተሸከርካሪዎች ዉስጥ 80 በመቶ ያህሉ የደህንነት መጠበቂያዎቻቸው የማይሰሩና የአየር በካይ የሆኑ ናቸዉ ብለዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም እንዳወጣዉ ሪፖርት አሮጌ ተሸከርካሪዎችንም አስመጪዎችም ሆኑ ተቀባዮች በጋራ አህጉሪቷን ለአየር ብክለት እየዳረጓት እንደሆነ ገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 104 ጥቅምት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here