አቢሲኒያ ባንክ 24ኛው አመታዊ መደበኛ የባላክሲዮንች ጠቅላላ ጉባኤውን ባካሄደበት ጊዜ እንዳስታወቀው አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘቡ ባለፈው አመት ከነበረው 32.15 የነበር ሲሆን ዘንድሮ 47 ነጥብ 63 ቢሊየን ማድረሱን አስታወቋል።
የባንኩ የካፒታል መጠን ደግሞ ከብር 4 ነጥብ 95 ቢሊየን በ14.7 በመቶ በማሳደግ ወደ ብር 5 ነጥብ 68 ከፍ ማድረግ መቻሉም ተገልጿል። ባንኩ ባለፈው ዓመት 14 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 16 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ገልጿል።
የጭማሪው ዋና ምክንያቶች በበጀት አመቱ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን አዳዲስ ደንበኞችን በመሳቡ መሆኑን ባንኩ በጉባኤው ላይ አስታውቋል።
በተጨማሪም ባንኩ ባለፉት 12 ወራት ከ1 ቢሊዮን በላይ ብር ያልተጣራ ትርፍ ማግኝቱን የገለጸ ሲሆን ትርፉ ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር የ6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ።
በተያያዘም አቢሲኒያ ባንክ በአዲስ አበባ ለዋና መስሪያ ቤት የሚያገለግል ባለ 60 ወለል ህንጻ 9 ሺህ 763 ካሬ ሜትር ስፋት ቦታ ሊገነባ መሆኑን ገልጿል።
ባንኩ ደንበል ሕንጻ አካባቢ የነበሩት ሁለት ይዞታዎች ለኦሮሚያ ክልል መንግስት ፕሬዝዳንት ማስፋፊያ ግንባታ በማስረከቡ አዲሱ ህንጻ የሚገነባው በምትክነት በተሰጠው ቦታ ላይ መሆኑም ገልጿል ።
ህንጻው የሚገነባውም በአዲስ አበባ ልደታ ክፈለ ከተማ ፣ ሜክሲኮ አደባባይ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ጎን የሚገኝ ቦታ ላይ መሆኑን አስታውቋል።
እስከ 60 ወለል የሚኖረው ህንጻ ግንባታ ላይ ለመሳተፍ አለም አቀፍ ተቋራጮች የፍላጎት ማሳወቂያ ሰነድ ማቅረባቸውም ተነግሯል ።
ይህንን ተከትሎ ባንኩ የጨረታ ሰነድ በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ሰምተናል።አቢሲኒያ ባንክ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘቡ 47 ነጥብ 63 ቢሊየን ብር መድረሱንም አስታውቋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 107 ኅዳር 12 2013



