ለታገዱት 38  ድርጅቶች ገንዘብ ገቢ ማድረግ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በባንክ በኩል እንዲፈጽም ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አሳሰበ

0
636

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሽብር ጥቃት እና ዘርን መሰረት ያደረገ ኹከት እና ብጥብጥ እንዲነሳ በማድረግ ሂደት ውስጥ እንዲሁም ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ በተፈጸመ ህገ-ወጥ ተግባር ውስጥ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ በወንጀል ተግባር ተሳትፈዋል በሚል ተጠርጥረው ምርመራ የተጀመረባቸው ከህወዓት ጋር ግንኙነት ያላቸው 38 ድርጅቶች መታገዳቸው ይታወቃል፡፡

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በመግለጫው ላይ እንዳለው ‹‹ የድርጅቶቹ የባንክ ሂሳብ መታገዱን ተከትሎ ለድርጅቶቹ ገቢ የሚሆኑ ገንዘቦች በባንክ በኩል መከፈሉ ቀርቶ በእጅ ለእጅ ወይም በካሽ (በጥሬ ገንዘብ) እንዲከፈላቸው የሚጠይቁ እና የሚቀበሉ የታገዱ ድርጅቶችን አመራሮች እና ክፍያውን በዚሁ መልክ የሚፈጽሙ ግለሰቦች እና ተቋማት እንዳሉ ደርሰንበታል፡፡›› ብሏል

 

‹‹ድርጊቱ የምርመራ ስራውን የሚያደናቅፍ፣ ለግብር ስወራ ወንጀል ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር እና ከብሄራዊ ባንክ መመሪያ ድንጋጌዎች ጋርም የሚጋጭ እና በህግ የሚያስጠይቅ ተግባር በመሆኑ የድርጅቶቹ አመራሮች እና ሰራተኞች እንዲሁም በዚሁ መልክ ክፍያዎችን እየፈጸማችሁ ያላችሁ ግለሰቦች እና ድርጅቶች ከድርጊታችሁ እንድትቆጠቡ እያሳሰብን በድርጊቱ የሚሳተፉ ግለሰቦችን እና ድርጅቶችን በምርመራ አጣርተን በህግ እንዲጠየቁ የምናደርግ መሆኑን እንገልጻለን›› ሲልም ጨምሮ ገልጿል፡፡

‹‹ማንኛውም ወደ ታገዱት ድርጅቶቹ ገንዘብ ገቢ ማድረግ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በባንክ በኩል እንዲፈጽም እያሳሰብን የሚኖሩትን ጥያቄዎች እና ጥቆማዎች ለተቋማችን ማቅረብ የሚችል መሆኑን አክለን እናሳውቃለን ›› ሲል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በፌስቡክ ገጹ ላይ አስታውቋል፡፡

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here