ልደቱ አያሌው ለታህሳስ 2 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጣቸው

0
387

ክሱ ከ‹ሕገ መንግሥቱን ለመገልበጥ ሙከራ› ወደ ‹ሕገ መንግሥታዊ ስርዓትን ማፍረስ› ተቀይሯል

ልደቱ አያሌው በተከሰሱበት ጉዳይ ከዚህ በፊት የቀረበው ክስ ላይ ጠበቃቸው የክስ መቃወሚያ በማቅረብ እንዲሻሻል ጥያቄ አቅርበው የነበረ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱም ዐቃቤ ሕግ ክሱን አሻሽሎ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ማስተላለፉ ይታወሳል።

በዚህም መሰረት በዛሬው ዕለት ኀዳር 24/2013 ዐቃቤ  ሕግ የተሻሻለውን ክስ ይዞ ቀርቧል።

 

ተሻሽሎ የቀረበው ክስ መጀመሪያ ከቀረበው ክስ ገዝፎ መምጣቱን የልደቱ አያሌው ጠበቃ አብዱልጀባር ሁሴን ለአዲስ ማለዳ የገለጹ ሲሆን፣ ክሱም ሕገ መንግሥቱን ለመገልበጥ ሙከራ ሲያደርግ ነው የተያዘው ከሚል ወደ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓትን አፍርሷል ወደሚል መቀየሩን ጠቅሰዋል።

አብዱልጀባር አያይዘው፣ ከዚህ ቀደም ፍርድ ቤቱ የተለያዩ ነጥቦችን ዘርዝሮ ክሱ እንዲሻሻል ትዕዛዝ መስጠቱን በማስታወስ በትዕዛዙ መሠረት ክሱ ተሻሽሏል ወይስ አልተሻሻለም? እንዲሁም አሁን የቀረበው ክስ ላይም ቢሆን ሊነሱ የሚችሉ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያዎች ስለሚኖሩ እነርሱን ለማቅረብ ነገ ጠዋት ወይንም ከሰዓት (አርብ ኅዳር 25) ቀጠሮ እንዲያዝልን ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

ዐቃቤ ሕግም በበኩሉ ጠበቃው ያቀረቡትን ጥያቄ ባለመቀበል ‹‹ነገ አልችልም ሰኞ ይደረግልኝ›› የሚል ክርክር አቅርቦ እንደነበርም አስታውቀዋል።

ፍርድ ቤቱ ግን የኹለቱንም ሐሳብ ውድቅ በማድረግ ተሻሽሎ በቀረበው ክስ ላይ ያላቸውን አስተያየትና ሌሎች የመብት ጥያቄዎችን እንዲያቀርቡ ለታህሳስ 02 ቀን 2013 ቀጠሮ መስጠቱን አብዱልጀባር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here