መስዑድ ገበየሁ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት ዳሬክተር ናቸው።
ኅብረቱ ሕጋዊ ዕውቅና አግኝቶ መንቀሳቀስ የጀመረው መጋቢት 2010 ሲሆን ለምስራታው መንስኤ የሆነው የቀድሞው የበጎ አድራጎት ማኅበራት አዋጅን በሰብኣዊ መብቶች፣ በዴሞክራሲ እና ግጭት አፈታት ዙሪያ የሚሠሩ ሲቪክ ድርጅቶች የነበራቸው አቅም እየተዳከመ በመምጣቱ እንዲሁም አብዛኞቹ ተቋማት ወደ መፍረስ ደረጃ እየተንደረደሩ ስለነበር ይህን ለመታደግ እና የጋራ ድምጽ ለመሆን ሲባል መሆኑን መስዑድ ይናገራሉ።
ዘንድሮ ለ72ኛ ጊዜ በዓለማቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የሰብኣዊ መብቶች ቀን ታኅሣሥ 1 (‘ዲሴምበር 10’) ምክንያት በማድረግ በሰብኣዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ የሲቪል ማኅበራት ኅብረት ከኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመተባበር ከኅዳር 22-30/2013 የቆየ የተለያዩ መርሃ ግብሮች ተካሂደዋል። ከተዘጋጁት መርሃ ግብሮች መሀከል ለታራሚዎች እና የማረሚያ ቤቶች ጥበቃ አካላት ስለ ሰብኣዊ መብቶች ሰፊ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች፤ በጋምቤላ ከተከፈጸሙት የመሬት መብት ጥሰት ጋር የሚያያዝ ዘጋቢ ፊልም ለእይታ ቀርቧል፤ ሲቪል ማኅበራት እና መገናኛ ብዙኀን በጋራ የሰብኣዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚያሥችሉ የተቀናጀ ግንኙነት እንዲፈጥሩ ያለመ ዝግጅትም ተካሂዷል። በተጨማሪም ዓለማቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀንን በማስመልከት ግጭቶች በአካል ጉዳተኞች ላይ ያላቸውን አስከፊ ገጽታ ለማሳወቅ እና ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ የማስገንዘቢያ ዝግጅት እንዲሁም በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ጽሑፎችን የሚያቀርቡ ጸሐፊዎችም ይሁን ‘አክቲቪስቶች’ ግጭት ቀስቃሽ ሆነው ከመቅረብ ይልቅ ሰብኣዊ መብቶች መከበር ላይ ሊጫወቱ የሚችሉትን ሚና በተመለከተ ሙያዊ ማብራሪያና ውይይቶች ከባለድርሻ አካላት ጋር ተካሂዷል።
ዓለማቀፉን የሰብኣዊ መብቶች ቀን ምክንያት በማድረግ እንዲሁም ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የአዲስ ማለዳው ይርጋለም ጸጋዬ ከመስዑድ ገበየሁ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።
የሰብኣዊ መብቶች ሳምንትን በማስመልከት የቀረቡት መርሃ ግብሮች ፋይዳቸው ምንድን ነው?
በእነዚህ መድረኮች የተገኘው ውጤትም ሲመዘን በተናጠል ይሠሩ የነበሩ የሰብኣዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች በጋራ የሚሠሩበት ሁኔታን ፈጥሯል። የሰብኣዊ መብቶች ጉዳይ በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት እንዲያገኝ ማድረጉ እንዲሁም በመገናኛ ብዙኀን እና የኪነ የጥበብ ባለሙያዎች በሰብኣዊ መብቶች ጥሰት ሰዋዊ የሆኑ ቀለማት ያለቸው የግንዛቤ መማስጨበጫ ሥራዎች እንዲሠሩ ጥሩ የማስተባበር እና የማነሳሳት አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በእነዚህ ዝግጅቶች ላይ የእናንተ ተሳትፎ በዋናት ምንድን ነበር?
ኅበረቱ ዋና አዘጋጅና አስተባባሪ ይሁን እንጂ በርካታ ተቋማት አብረውን በዚህ ዝግጅት ላይ ተሳትፈዋል። ለአብነት ያህልም የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምስራቅ አፍሪካ ጽሕፈት ቤት፣ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች፣ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የሰብኣዊ መብቶች ማዕከል ተሳታፊዎች ናቸው።
ጥያቄ፡-የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች በኢትዮጵያ ምን ዓይነት ገጽታአላቸው?
በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲፈጸሙ ቆይተዋል። በተለይም በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሁሉ ሳይቀር ዜጎች ለሰብኣዊ መብት ጥሰቶች ሲዳረግ ቆይቷል። ከለውጡም በኋላ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች መልካቸውን ቀይረው የብሔር ማንነት ላይ በማተኮር፣ እምነት እና ሌሎች ጉዳዮችን በማስመርኮዝ ለበርካታ ጊዜያት ሲደጋገሙ ተስተውለዋል። በተላይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፖለቲካው መካረር ከትንንሽ ግጭቶች ባለፈም ወደ ለየለት እና እጅግ አስከፊ የሆኑ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን ለማየት ተችሏል።
የፌደራል መንግሥቱ እየወሰደው ባለው ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ ውስጥ የሰብኣዊ መብት አያያዝ ላይ ምን ገጽታ ነበረው?ምንስ ለማድረግ ችላችኋል?
በፌደራል መንግሥቱ እና የሕወሓት መሃከል በሚደረገው ሕግ የማስከበር ሥራ ሊኖር የሚችለውን የሰብኣዊ ምብት አደጋ ከወዲሁ ለመቀነስ ከሌሎች ስምንት የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት ጋር በመሆን ኹለቱም አካላት በጦር መሣሪያ ከሚደረግ እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ እና በአካባቢው ያለውን የማኅበረሰብ ክፍል ወደ አልተፈለገ የሕይወት አቅጣጫ ከመጨመራቸው በፊት ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ የሚያልቅበትን መንገድ ቅድሚያ ሰጥተው እንዲወያዩበት ሐሳብ አቅርበን ነበር።
ይህን ያልንበት ዋና ምክንያት ደግሞ ግጭቶቹ በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚያሳርፉት አሉታዊ ተጽእኖ በተለይም የዜጎች ሕይወት መቀጠፍ ፣የእምንት ተቋማት መውደም፣ የትምህርት ቤቶች መፈራረስ እና የመሰረተ ልማት ተቋሞች ከጠቅም ውጪ መሆን በቀጣይ ሕየወትን የሚ ያከብድ የእለት ከእለት ሕይወትን ወደ አዘቅት የሚከት በመሆኑ ነው።
ምን ዓይነት ችግሮች አጋጥመዋችሁ ነበር?
ይህን በምናደርግበት ወቅት ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኖብን የነበረው መረጃ የማገኘት ችግር ነበር። በኹለቱም በኩል የነበረው የ መረጃ አቅርቦት በቂ የሚባል ስላልነበር እና በተለይም በትግራይ በኩል ምንም ዓይነት ዕድሉ ስላልነበረ የችግሩን ስፋት ለማወቅ እና የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን ለመረዳት ተጽእኖ አሳድሮብናል።
በዚህ ዙሪያ የፌደራል መንግሥቱ በንጹሃን ዜጎች ላይ ምንም ዓይነት አደጋ በማያስከትል መልኩ ሕግ የማስከበር እርምጃው የወሰደ ቢሆንም ምንም ዓይነት ችግር አለተፈጠረም ማለት አይቻልም።
በዚህ የግጭት ወቅት የነበረው የሰብኣዊ መብት ጥሰት ቀላል ተብሎ የሚታለፍ ዓይነት አልነበረም።እንደ ማኅበረሰብ በዚህ ደረጃ ኢሰብኣዊ የሆኑ ድርጊቶችን ለመፈጸም የሞራል ዝቅጠት ላይ መደረሳችን በራሱ እጅግ አሳፋሪ ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ አለበት።እንደ አጠቃላም በግጭቱ ወቅት የተፈጠሩት የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች እጅግ ከባድ እና ብዙ ቢሆኑም ሁሉንም ይፋ ማድረግ የሚቻለው የምርመራ ውጤቱ ሲጠናቀቅ ነው።
እንደ አጠቃላይ ለመግለጽ ያህል ግን ብዙ ችግር ተከስቷል ሊባል ችላል።በክልሉ ውስጥ ያሉ አካል ጉዳተኞች ፣ሕጻናት፣ ሴቶች እና አዛውንቶች ሰብአዊ ኢኮኖሚያዊ እና ለከ ባድ ሥነ ልቦናዊ ቀውስ እንግዲህ የህ እና ይህን መሰል የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች የቅድመ ምርመራው በኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን የቅድመ ምርመራ ሥራ ተከናውኗል።
የግጭቶች መበራከት እና የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች መበራከት ለውጡን ተከትሎ የመጣ ነገር ነው ተብሎ ይታሰባል፤ ኅብረቱ በዚህ ላይ አስተያየት አለው?
የግጭቶች መበራከትም ይሁን እየከፉ መምጣት ከለውጡ ጋር ብቻ ተያያዥነት አላቸው ብዬ በግሌ አላምንም ።ከለውጡ በፊትም እጅግ ኢሰብኣዊነት የተ ሞላባቸው ድርጊቶች ሲፈጸሙ እንደነበር ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል፤ብዙ ሊባልባው ያለተቻለው በወቅቱ ከነበረው የአፈና ሥርዓት አንጻር ነው እንጂ የሚሠሩ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች ሳይኖሩ ቀርተውአየደለም።ምንአልባትም መንግሥታዊ መዋቅሩ ሳይቀር በሰብኣዊ መብት ጥሰቱ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ችሏል፤ማረሚያ ቤቶች ከፍተኛ ኢሰብኣዊ መብት መጣሻ ቦታችዎች ሆነው አገልገለዋል፤የፖለቲካ አመለካከቶች ሌላኛው የሰብኣዊ መብት ጥሰት ሰለባዎች ነበሩ ማለት ይቻላል።
ከለውጡ በኋላ የተፈጠሩት ግጭቶችን ስንመለከታቸው የትኛውም ግለሰብ፣ቡድኖችም ይሁኑ ስብስቦች እንደዚህ ዓይነት ድርጊት ለመፈጸም ዕድሉ አልነበራቸውም ።ከለውጡ በኋላ ግን የአፈና ስርዓቱ እየላላ በመምጣቱ ብዙ ሊባሉ የሚችሉ ችግሮችን ለማየት ተችሏል፤ጠቅላይ ሚንስተሩም በመገለጫቸው እንዳብራሩት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እጅግ ብዙ ሊባሉ የሚባሉ ግጭቶች በተለያዩ ክልሎች እና ቡድኖች አማካኝነት ተፈጽመዋል።
ማይካድራ ላይ የተፈጸመው የሰብኣዊ መብት ጥሰትኢትዮጵያን ይገልጻታል ብለው ያምናሉ?
በማይካድራ የተፈጸመውን አሰቃቂ የሰብኣዊ መብት ጥሰት እንደ ግለሰብም ሆነ እነደ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ የፈጸመል ብሎ የሚገምት ዜጋ ያለ አይመስለኝም፡፡ከኢትዮጵያ አብሮ መነር ሥነ ልቦና እና ማኅበራዊ ትስስር አንጻር ህን ኢሰብኣዊ ድርጊት ለመፈጸም የሚያስችል የሞራል ዝግጅት አለን ብሎ ለማሰብ የሚከብደ ነው፡፡የኢትዮጵያ ሰብኣዊ ኮሚሽን ባቀረበው ቅድመ ምርመራ ላይ የተመለከትነው ድርጊት የቱንም ያህል የዘርም ይሁን ሌላ ጉዳይ በዚህ ደረጃ ዜጎችን ፍጹም ዘግናኝ በሆነ ኢሰብኣዊነት ለማጥቃት የሚያስችል ሰበብ የኖራል ብሎ ለማሰብ አያስደፍርም፡፡
ኅብረቱ ምን ዓይነት መፍትሄ አለ ብሎ ያምናል?
የኅብረቱ ዋና አጀንዳ ግን ማን ምን አደረገ የሚለው ሳይሆን በዜጎች ደህንነት ዙሪያ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበት የፌደራል መንግሥት ሕግን በማስከበር ፣የዜጎችን ደህንነት በመጠበቅ፣የአገርን ሕልውና በማረጋገጥ እና አስተማማኝ ሰላምን ለማረጋገጥ የኃይል እርምጃ በመውሰድም ቢሆን ሊሄደበት የሚገባ ጉዳይ ነው።ምክንያቱም ኃይልን የመጠቀም ብቸኛ ሥልጣን ያለው መንግሥት ሥለ ሆነ ለዜጎች ደህንነት እና ሰላማዊ ሕይወት ሲባል በየትኛውም አግባብ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ። ከዚህም ባለፈ የዜጎችን ሰብኣዊ መብቶች ለአደጋ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች መጠበቅ መቆጣጠር ይኖርበታል፡፡
እንደ ሲቪል ማኅበራትም ይሁን እንደግለሰብ የምናምነው ሕግ የማስከበር ጉዳይ ፤የብሔራዊ ሉአላዊነት ጉዳይ ነው። በመሆኑም የፌደራል ምንግሥቱ ሕግን ከማስከበር አንጻር ሲያደርግ የነበረው እና እደረገውም ያለው ነገር ሕዝባዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንጻር ሊታይ ይገባል።ማንም ይሁን ምን በሕግ እና በሕግ ብቻ ነው ሊዳኝ የሚችለው፤ሕግ እና ሕገ መንግሥታዊ መርሆችን ልናከብራቸው እንሁም ልንገዛላቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው።
ቅጽ 2 ቁጥር 110 ታህሳስ 3 2013



