ሌተናል ኮሎኔል ፍሰሀ በርሔ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ በጤና ባለሙያነት ያገለገሉ የጦር መኮንን ናቸው። በቀድሞው አጠራር ራያ እና ቆቦ አሁኑ ደቡብ ትግራይ ውስጥ በሚገኘው አላማጣ የተወለዱት ፍሰሀ፥ በወቅቱ የደርግ አምባገነንነት አስገድዷቸው በ1981 ወደ ትጥቅ ትግል ገብተዋል፤ ከደርግ ውድቀት በኋለም በመከላከያ ውስጥ የሕክምና ትምህርት ተከታትለው የአንድ ሻለቃ ሕክምና ኀላፊ ሆነው አገልግለዋል።
የቤተ መንግሥት ጥበቃ የወጋገን ሻለቃ ሕክምና ኀላፊ በነበሩበት ወቅትም ወደ ሩዋንዳ በመዝመት በሰላም ማስከበርላይ ተሳትፈዋል። በወቅቱም ከአሁኑ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በአንድ ላይ እንደዘመቱም ኮሎኔል ፍሰሀ ይናገራሉ።
ከሰላም ማስከበር ዘመቻ መልስም የትምህርት ዕድል አግኝተው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በጤና መኮንንነት ሠርተዋል፤ በተመሳሳይ ዘርፍ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ የውድድር በር ተከፍቶላቸው ኹለተኛ ዲግሪያቸውን ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ሠርተዋል። በኋለም የቀዶ ጥገና ትምህርት (field Surgeon) የሰለጠኑት ፍሰሀ፥ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት በተግባር ሙያዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል። አሁንም ሙያቸውን ለማሳደግ በጤና መኮንንነት የዶክትሬት ትምህርት በመከታተል ለመጨረስ ጫፍ የደረሱ እጩ ዶክተር ናቸው።
የወታደር ሕይወት የተሰጠውን ግዳጅ መፈጸም በመሆኑ የኹለተኛ ዲግሪያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ዛላንበሳ ግንባር ተመድበው የሰሜን ዕዝ ክፍል የሆኑትን የ13ኛ፣ 23ኛ እና 43ኛ ክፍለ ጦሮችን በሙያቸው አገልግለዋል፤ ኀላፊነታቸውንም ተወጥተዋል።
ኮሎሌል ፍሰሀ በ1997 ወደ መከላከያ ሚኒስትር ዋና መሥሪያ ቤት በመከላከያ ዋና መምሪያ የኤች አይ ቪ ቢሮ ማርች ፕሮጄክት አስተባባሪ ሆነው ከማገልገል ባሻገር፥ በመከላከያ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት ሠርተዋል። በተጨማሪም በሱዳን የተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ አባል በመሆን በተራ ወታደርነት (‘ኮንቲንጀንት’) አገራቸውን አገልግለዋል።
በሰላም ማስከበሩ ተልዕኮ መሳተፌ የሰው ኀይል አመዳደብን በተመለከተ የሕወሓት’ን የጥቅም ትስስር እና ሸፍጦች እንዳይ ዓይኔን ገልጦልኛል የሚሉት ፍሰሀ፥ በገንዘብ ለመጥቀም በተደጋጋሚ ከሚላኩ አባላት በተጨማሪ በተለይ ሚሊዮኖች የሚታፈስበትን ታዛቢ (‘ኦብዘርቨር’) ሆነው የሚላኩት በትስስሩ መረብ ውስጥ የሚገኙት ብቻ ናቸው በማለት የሚደረገውን መድሎ ይገልጻሉ።
በመከላከያ ተቋም ውስጥ ያለው ሙስና እና ብልሹ አሠራር በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም የሚሉት ፍሰሀ፥ በተለይ የቅርብ አለቃቸው የነበሩት ጀነራል ከመከላከያ ዕቃ ማከማቻ ግምጃ ቤት በተለየ በቢሯቸው የራሳቸውን መጋዘን በማዘጋጀት በተለይ ከውጪ በግዢም ይሁን በእርዳታ የሚመጡ ከኤች አይ ቪ ጋር የተያያዙ የሕክምና ቁሳቁሶችን ለግል ጥቅም ያውሉት ነበርም ሲሉ ከአዲስ ማለዳው ኤርሚያስ ሙሉጌታ ጋር ባደረጉት ቆይታ አጋልጠዋል።
እንዴት ነበር ከመከላከያ የተሰናበቱት?
በ2004 አለቃዬ ወደ ቢሮው አስጠርቶኝ ሱዳንም ሄደህ የሠራዊቱን መልካም ሥምና ዝና አጥፈተሃል፤ አለቃም አትታዘዝም። ይሁንና ፤ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ አሰገባ በተባልኩት መሰረት እንዲህ በቀላሉ ሠራዊቱን እንድሰናበት ተደረኩ። ለጀነራል ሳሞራ ኑስ አራት ጊዜ ደብዳቤ ጽፌለት ስለጉዳዩ ባስረዳውም ምንም ምላሽ ሊሰጠኝ ፈቃደኛ አልነበረም። እንዲያውም እኔን የሚቀርቡኝ እና ደህና አመለካከት የነበራቸው ጀነራሎች ምን አለፋህ ከግራ ወደ ቀኝ ኪስ ለሚገባ ደብዳቤ ለምን ጊዜህን ታባክናለህ ይሉኝ ነበር።
አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ ነው ያሉት?
አሁኑ ጀነራል ሀጫሉን እንዲሁም በመከላከያ በጤና መምሪያም ያሉ ሰዎችን አነጋግሬያለሁ፤ መጎዳቴን እና ፍትሐዊነት በጎደለው መልኩ መሰናበቴን በመገንዘባቸው በታዛቢነት ሊልኩኝ ቃል ገብተውልኛል። ቅድሚያ ለማን እንደሚሰጥ ግንው አይታወቅም።
እርስዎ የተሰናበቱት እነ ጀነራል አበባውም ተሰናበቱበት ወቅት ነበር?
አዎ! ያን ጊዜ እኮ ሌ/ጀ አበባውን ጨምሮ በርካታ ጀነራሎች እና ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የተሰናበቱበት ወቅት ነበር። በሦስት የተለያዩ ዙሮች ነበር ያሰናበቱትን። አብዛኛውን በብቃት ማነስ እና ጡረታቸው የደረሰ በሚል ነበር እንድንቀነስ ያደረጉት። ነገር ግን ከእውነት የራቀ ነው፤ ምክንያቱም ጀነራል አበባው ምርጥ ወታደራዊ አመራር ነው፤ ጄነራል ባጫም እንደዛው የተዋጣለት ወታደር ነው። ከተሰናበቱት ጀነራሎች አብዛኛውን የሚሸፍኑት የአማራ ብሔር ተወላጅ ጀነራሎች ናቸው። እነርሱ በዘር ከፈሉት እንጂ የአማራ፣ የትግሬ ወይም የኦሮሞ የሚባል ጀነራል የለም፤ የኢትዮጵያ ጀነራል ነው ያለው። ጀነራል አበባው ኢታማዦር ሹም ተብሎ ሳሞራን ይተካል ተብሎ ሲጠበቅ እና በእርግጠኝነት ሲታሰብ የነበረ ጀነራል ነበር።
በሕገ መንግሥቱ ውስጥ መከላከያ ከፖለቲካ የጸዳ እንደሆነ ያስቀምጣል። ይህ በተግባር እንዴት ይገለጻል?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድብዙ ጊዜ የሚያነሱት ቀይ መጽሐፍ አለ። በእርግጥም ይህን መጽሐፍ ሕወሓት ነው ያጸደቀው። መጽሐፉ መከላከያው ስርዓቱን፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ጠባቂ ነው ብሎ በግልጽ ያስቀምጣል። መከላከያው ከትኛውም የፖለቲካ ስርዓት ነጻ እና ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኝነት የጸዳ መሆን አለበት። ይሁንና ሕወሓት መከላከያን የእኛ ነው ብለው ነው የሚወስዱት። መጽሐፉመከላከያ ሠራዊት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ እንዲመራ ያዛል።
ኢሕአዴግ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ስለሚመራ እና መከላከያውም የኢሕአዴግ ደጋፊ ነው ማለት ነው። ስለሆነም ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚወጣ አባል እንዲገለል ይደረጋል። ለሕወሓት ኢትዮጵያ ማለትን እንደ በሽታ ነው የሚቆጥሩት፤ ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል መስማትም ሆነ መጥራት አይችሉም። ዐቢይ እኮ የተወደደው ኢትዮጵያ ስላለ እንጂ በሌላ አይደለም። ኢትዮጵያ ስላለ ሁሉንም ማነሳሳት ችሏል፣ ታፍና ነበረችው ኢትዮጵያ እንድታንሰራራ አድርጓል። ስለዚህ መከላከያ ከፖለቲካ እና ፓርቲ ውጭ መሆን አለበት።
በነገራችን ላይ መከላከያ ብቻም ሳይሆን የአገሪቷ ስርዓት በራሱ በሕወሓት የተመራ ነው የነበረው።
ከተለያዩ ክልሎች ለሚመጡ እና ወደ መከላከያ ለሚገቡ ሰዎች የተለያዩ ሥያሜዎች ሲሰጣቸው ይታወቃል። በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ መከላከያ አባላት በድንገት ሊታሰሩ እና ሊሰወሩ የሚችሉበት አጋጣሚም አለ። ከዚህ ጋር ተያይዞ በሰሜን ዕዝ አለ ስለሚባለው ድብቅ እስር ቤት እና ስለ ዕዙም ቢነግሩን
እውነት ነው ከአማራ ክልል የሚመጣውን ግንቦት 7፣ ከኦሮሚያ ለሚመጣው ደግሞ ኦነግ እንዲሁም ተግራዋይ ሆኖ ለሕወሓት የማይመቸውን ደግሞ ደምኢት ወይም ደግሞ ሻዕቢያ እያሉ ሲያሸማቅቁት ኖረዋል። በነገራችን ላይ ሕወሓት ለጥፋት በጣም ጎበዝ ስትራቴጂ የሚነድፍ ድርጅት ነው። ሰው ለማጥፋት በጣም ጥበበኛ ድርጅት ከመሆኑም የተነሳ ገድሎ እኮ አብሮ ሬሳ ያፈላልግሀል። እከሌ የሚባል ግለሰብ አላሥራን ብሏል ተብሎ ይገደል ተብሎ በኹለት እና ሦስት ሰዎች ይወሰናል። ከዛም ይገደላል በመጨረሻም ይሄ ሰው የት ጠፋ ተብሎ ይፈለጋል። ሕወሓቶች ሥም በመለጠፍም የተካኑ ናቸው። ለምሳሌ ከኦሮሞ ብሔር የሆነ ወታደር ካልተመቻቸው ይሄ ሰው ከኦነግ ጋር የተያያዘ ጉዳይ አለው፤ መረጃም አግኝንተንበታል ይሉና በቤቱ ውስጥ ወረቀት በማስቀመጥ ፖሊስ ወረቅቱን አንሳው ብሎ በማስገደድ ፎቶ ያነሳል፤ ይህም ለክሱ እንደማስረጃ ሆኖ ይቀርባል።
ሌላው ከሰሞኑ የሰሜን ዕዝን በተመለከተ በጣም የሚሳዝን ጉዳይ ነው። በእርግጥ ከለውጡ ጀምሮ ኢትዮጵያ አደጋ ላይ የነበረች ስትሆን ምክንያቱ ደግሞ ሕወሓት ነው። ኢትዮጵያ በዓባይ ጉዳይ ከግብጽ ጋር ፍጥጫ ውስጥ ባለችት ሁኔታ፣ ጠቅላይ ሚንስትሩም እንዳሉት በተለያዩ ኢትዮጵያ ክፍሎች የተከሰተው 113 ግጭቶች፣ የተፈጥሮው አደጋ እና መሰል ችግሮች ባሉበት ሁኔታ፥ ሕወሓት ይህን ዓይነት ጥቃት መሰንዘሩ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው። አገራችንን ከውጭ ጥቃት ለመከላከል እየተንቀሳቀስን ባለንበት ሁኔታ ጥቃቱ ከውስጥ መፈጸሙ ያሳዝናል።
በጥቅምት 24ቱ የሰሜን ዕዝ ጥቃት የውጭ አካላት እጅ አለበት ብለው ያስባሉ?
በሚገባ አለው እንጂ! ይህ ጉዳይ እኮ የቆየ እና የተቀናጀ ጥቃት ነው። እንዲያውም ደብረጺዮን እኮ በአንድ ወቅት ቃለ ምልልስ ሲያደርግ ዐቢይ የውጭ ኀይል የሚያመጣ ከሆነ፥ እኛም ማምጣት እንችላለን የሚል ንግግር ሲያሰማ በጆሮዬም አድምጫለሁ። “ማነው የውጪው ኀይል?” ያው አንድ ግብጽ ናት፤ ነገር ግን ኔትዎርካቸው በእጅጉ ብዙ እና ውስብስብ ስለሆነ ሌሎችም ሊኖሩ ይችላሉ። ዐቢይም የተቸገረው በዚህ ሊሆን ይችላል። የሕወሓት ከግብጽም ሆነ ከሌሎች ጋራ የፈጠረው የክፋት ትስስር ይሄ ነው የሚባል አይደለም።
ከግብጽ ጋር ግን የተጠናከረ ይመስለኛ። [ዓባይ] የግብጽ የህልውና ጉዳይ ስለሆነ መሰለፏ ብዙም አይገርምም። ዓላማው ደግሞነ ለሕወሓት እርዳታ በማድረግ በኢትዮጵያ ውስጥ ኹከትን ለመፍጠር ነው። ከኦነግ ሠራዊት ጋር በተደረገ ውጊያ እኮ የሕወሓት አባላት ተይዘዋል። ይህ ታዲያ እንዴት ትስስራቸው ለመዘርጋታቸው ማሳያ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።
ሕወሓት ከውጊያው በፊት እኮ ክፍተኛ ፕሮፖጋንዳቸውን ሲለቁ ነበር። እኔ በበኩሌ ኢትዮጵያ እና ትግራይ የሚባሉ ኹለት አገራት አሉ ወይ ወይ ስል ሰንብቻለሁ። እኔ በበኩሌ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን የምተቸው እንዴት ኹለት ዓመት ሙሉ ዝም አላቸው በሚል ነው። በግሌ የለውጡ ደጋፊ ነኝ፤ ነገር ግን እነዚህ ሰዎችን ባህሪያቸውን እያወቀ ለምን ዝም ይላቸዋል? እንዴት 30 እና 40 ሰዎችን አስሮ አያመጣም? እንደዛ ቢደረግ እና አሁን ያለው ውጊያ ወይም ደግሞ አሁን ያለው አጋጣሚ አይፈጠርም ነበር።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ዙሪያ ምን ይላሉ?
በመጀመሪያ ወራት አካባቢ ጠቅላይ ሚንስትሩ መታፈኖች እና እንደ ልብ አለመንቀሳቀስ ሊያጋጥማቸው ይችላል። ነገር ግን ጌታቸው አሰፋንም ሆነ ሌሎች የሕወሓት አባላትን በሚመለከት ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ ሳይሄዱ በፊት በመያዝ ለሕግ ማቅረብ ይችሉ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ሕዝብ መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ ደግፏቸው ነበር። ከዚህም ባለፈ ለስብሰባም ወደ መሐል አገር ይመጡ በነበሩበት ወቅት በቁጥጥር ሥር አውሎ አገር እስኪረጋጋ ድረስ ማቆየት ይቻል ነበር። እነርሱ ባይሄዱ እና በአንድ ላይ ሆነው ባይመክሩ ኖሮ እኮ ይሄ ሁሉ ጉዳይ አይመጣም ነበር። ሳሞራን እና ጌታቸውን ከሥልጣን ማውረዱ ይመስለኛል ትልቁ ሥራ። ሽማግሌዎቹን እንዴት ማሰር እና ለሕግ ማቅረብ እንዳቃታቸው ግራ ይገባኛል።
በመከላከያ ዋና መምሪያ ውስጥ ሆነው ከሕወሓት ጎን የተሰለፉም እንዳሉ እየሰማን ነው። ደግሞ የሬዲዮ መገናኛ መስመሮችን በመበጣጠስ ያገዙ መኮንኖችም እንደነበሩም በመንግሥት ተገልጿል። በዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?
በትግራይ ሁኔታ ላይ ሕወሓቶች ከመሐል አገር ከሔዱ በኋላ በጣም የተዘጋጁበት ጉዳይ ነው። እኔ መቐለ፣ አክሱም ሆቴል እና አክሱም ከተማ አይቻቸዋለሁ። በመጀመሪያ ወራት አንገታቸውን ደፍተው እና ተሸማቀው የነበሩ ሰዎች ነበሩ። ነገር ግን ኹለት እና ሦስት እጥፍ አልፈው የሚያስቡት ሕወሓቶች በተንኮላቸው በየገጠሩ ወጣቱን ለጦርነት እንዲነሳሳ ማድረግ ጀምረው ነበር። አጽቢ በሚባል ስፍራ በድብቅ ወጣቶችን ወታደራዊ ሥልጠና እየሰጡ እንደነበር ይታወቃል። በእርግጥ በሌሎች ስፍራዎችም ያሠለጥናሉ፤ ከዚህ የሔዱት ጀነራሎች በቀጥታ ወደ ሥራ ነው የገቡት። የኢትዮጵያ ጀነራል በዚህ ጉዳይ ላይ መሳተፋቸው በጣም ያሳዝናል። የአንድ ድርጅት አባል ሆኖ ኢትዮጵያን መልሶ መውጋት ወንጀል ነው።
እኔ በበኩሌ መቀሌ ሄደው ታስረዋል ይባል የነበረውን አልቀበልም። አሁንም እንኳን ተባረዋል ተብሏል። ይሁንና የሚተኙ ሰዎች አይደሉም። ስለዚህ ለእነዚህ ሰዎች ምንም ጊዜ መስጠት አያስፈልግም። ለሕወሓት ጊዜ መስጠትም ሆነ ወደ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ይመጣል ተብሎ በፍጹም የማይታሰብ ጉዳይ ነው። ሚስትህን እኮ የአንተ ደኅንነት በማድረግ አንተን እንድትሰልል የሚያደርጉ ሰዎች ናቸው። ሴቷን ሒጂ እና አግቢው እንዲያምንሽም ደግሞ ውለጂለት ብለው ባልን የሚያሰልሉ ሰዎች እኮ ናቸው። ከሐዲዎች እኮ በመከላከያ እንደነበሩት ሁሉ፤ ከተራ ወታደር ባለፈም ሻለቃዎች ከሕወሓት ጋር ላለመተባበር ወስነው ኀይላቸውን ይዘው ከወገን ሠራዊት ጋር አብረው ወደ ኤርትራም ያፈገፈጉ ነበሩ።
በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጠረውን አጋጣሚ እንዴት ይመለከቱታል? ድሮ በሕወሓት የትጥቅ ዘመን ስለዴሞክራሲ እንወያይ በሚል ከሌሎች የትግራይ ታጋዮች ጋር ቀን ስብሰባ ውለው ከአሁን በኋላ ለትግራይ ሕዝብ አብሮ ለመሥራት ተስማምተው እና ተግባብተው እራት ተበልቶ በተኙበት ለእያንዳንዱ ገዳይ ተዘጋጅቶ እና ምልክት ተሰጥቶ አስጨርሷቸዋል፤ ሰዎቹ አረመኔዎች ናቸው። እንግዲህ አስበው ወንድምህን እና ለዲሞክራሲ እንታገል ያልከውን ሰው ማጥፋት ማለት ከድሮውም የማፊያ አቋም ያላቸው ቡድኖች መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። ይህን በመመርኮዝ በቅርቡ በሰሜን ዕዝ ላይ ተፈጠረ የተባለው ጥቃት ሕወሓት ከተላበሰው ባህሪይ አንጻር የሚጠበቅ ነው። ሁላችንም እንደምናስታውሰው በሰሜን እዝ ያለውን የመከላከያ ኀይል ለማንቀሳቀስ መኪኖች በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ሕጻናት እና እናቶችን መንገድ ላይ በማስተኛት እዛቸውን እንዳይለቁ ሲያደርጉ ነበር። በእርግጥም ሕጻናቱንና ሴቶቹን የሚልካቸው ሕወሓት ነበር። ምክንያቱ ደግሞ መከላከያ ወደ ሕዝብ እንደማይተኩስ ስለሚያውቅ ነው። ከዛን ጊዜ ጀምሮ ታዲያ እኔም ስናገር ነበር። እነዚህ ሰዎች ትክክለኛ ነገር እየሠሩ አይደለም እያልኩ ስናገር ነበር።
የትግራይ ሕዝብ ማለት ሕወሓት ነው በሚል በሕወሓት በኩል ሲገለጽ እና ሲሠራበት ቆይቷል። በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ዓይነት አስተያየት አለዎት?
ይሄ ጉዳይ ሕዝቡ ታፍኖ እንጂ እንደሚባለው ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም። በአንድም በሌላም ሐሳቡን እና ልዩነቱን እንዳይገልጽ ስለተደረገ እንጂ ሕወሓትና ሕዝቡ አንድነት የላቸውም ።
በሰሜን ዕዙ ጥቃት ላይ የወታደራዊው መረጃ ክፍልሥራውን ተወጥቷል ማለት ይቻላል?
በእርግጥ ኢታማዦር ሹሙ ስለ መከላከያ እንዳይወራ እና መረጃዎች እንዳይሰጡ በይፋ አስጠንቅቀዋል። የወታደራዊ ደኅንነት መረጃን በሚመለከትም በትክክል ሥራውን ተሠርቷል ለማለት ያስችላል። ነገር ግን እኔ እንደሚገባኝ መረጃዎችን በተገቢው ሁኔታ እንዳይገኙ በብሔር እና በዘር ሕወሓቶች ሰዎችን በማጥመዳቸው ከመረጃ ሰዎችም ሊኖሩ ይችላሉ። በመሆኑም ጥቃቱን መከላከል አልተቻለም። ነገር ግን ይህ ማለት የመረጃ ክፍሉ በትክክል ሥራውን አልተወጣም ግን አያስብልም። ሕወሓት ጥቃቱን የፈጸመችው ሰዎችንም ካደራጀች በኋላ ነው ። ወታደሩ እኮ በጣም የሚያሳዝ ነው። ደሞዙን እያዋጣ ፤ዱቄት እና ዘይት ለሕዝቡ ሲሰጥ፣ አንበጣ ሲያባርር፣ እህል ከማሳ ላይ ሲያጭድ እየዋለ በደከመ ጉልበቱ በባልንጀራው እንዲገደል ማድረግ ምን ዓይነት ጭካኔ እንደሆነ መግለጽ ያስቸግራል። ጥቃቱ ከውስጥ እና ከውጭ መፈጸሙ ደግሞ ጉዳቱን የከፋ አድርጎታል። ድርጊቱ በእጅጉ የተጠና እና የታሰበበት ነው ለማለት ይቻላል።
ቅጽ 2 ቁጥር 110 ታህሳስ 3 2013



