ሱዳን ድንበሩን ጉዳይ በድርድር እንድትፈታ ጀነራል ብርሐኑ ጁላ ተናገሩ

0
944

ሱዳን በሶስተኛ ወገን የተደገሰላትን የጦርነት ወጥመድ ወደ ጎን በመተው የድንበሩን ጉዳይ በድርድር ለመፍታት ቁርጠኛ መሆን እንዳለባት የኢፌዴሪ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።
የትግራይ ህዝብ ጁንታው ተመልሶ እንደሚመጣ አስመስለው ባዶ ህልም በሚነዙ አካላት ሳይደናገር ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እያደረገ ያለውን ደጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ነው ያሉት።
ኢታማዦር ሹሙ ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ይህን ያሉት ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው።
ኢትዮጵያና ሱዳን የሚገጥማቸው የውስጥ ችግር ያልበገረው ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ ወዳጅነት እንዳለቸው አስታውሰዋል።
ከአንድ ዓመት በፊት ሱዳን የገጠማት ፖለቲካዊ ችግር ሱዳናዊያንን ሳይጎዳ በሰላም እልባት እንዲያገኝ በማድረግ የኢትዮጵያ ሚና ከፍተኛ ነበር ነው ያሉት።
ነገር ግን የኢፌዴሪ መንግስት በጽንፈኛው የህወሃት ጁንታ የህግ ማስከበር እርምጃ እየወሰደ ባለበት ወቅት የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር ጥሶ መግባት ጠቁመዋል።
ይህም አገራቱ ካለቸው ወዳጅነት አንጻር ከሱዳን የማይጠበቅ አሳዛኝ ተግባር ነው ብለዋል።
የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ድንበር ጥሶ ከመግባቱ ጀርባ የግድቡን ድርድርና ግንባታ ማስተጓጎልን ያለመ ሶስተኛ አካል መኖሩን ጠቅሰዋል።
ይህ አካል ኢትዮጵያ የህግ ማስከበር እርምጃ ላይ መሆኗንና ሱዳን ደግሞ ፖለቲካዊ ሽግግር ላይ መገኘቷን እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀሙንም ነው የተናገሩት።
ከዚህ በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢዎች የሚፈጠሩ ችግሮች አዲስ አለመሆናቸውንና በሰላም ሲፈቱ መቆየታቸውን ያስታወሱት ጀነራል ብርሃኑ፤ የአሁኑ ግን የሶስተኛ ወገን እጅ ስላለበት ችግሩ ጎላ ብሎ ወጥቷል ብለዋል።
ሆኖም ኢትዮጵያ ችግሩን በሰላም መፍታት እንጂ ከወዳጅ ሀገር ሱዳን ጋር ወደ ጦርነት መግባት እንደማትፈልግም ገልጸዋል።
ሱዳንም በሶስተኛ ወገን ከተደገሰላት የጦርነት ወጥመድ ወጥታ ችግሩን በድርድር ለመፍታት ቁርጠኛ መሆን እንዳለባትም ጥሪ አቅርበዋል።
በቅርቡም ጉዳዩን በሚመለከት በሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ ተቋሞች ደረጃ ንግግር ለማድረግ ቀጠሮ ተይዟል ብለዋል ጀነራል ብርሃኑ ጁላ።
በተያያዘ ዜና በመተከል የተጀመረው የህግ ማስከበር እርምጃ በዞኑ የሚንቀሳቀሰው ሽፍታ እንቅስቃሴ ከግምት ወስጥ ባስገባ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል።
ሽፍታው ካለው ባህሪ አንጻር እንቅስቃሴው የሚገታው የጸጥታ ተቋማት ከሚወስዱት እርምጃ በተጓዳኝ ጠንካራ መንግስታዊ መዋቅርና የህዝብ አደረጃጃት በመፍጠር መሆኑንም ነው ያነሱት።

ቅጽ 2 ቁጥር 116 ጥር 15 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here