የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ ፖሊስ የጋራ የፀጥታ ግብረ ኃይል ሊያቋቁሙ ነው
የኢትዮጵያና የጅቡቲ የፖሊስ ተቋማት ለመጀመሪያ ጊዜ የጋራ ዘመቻ መስራት የሚያስችላቸውን የጋራ የፀጥታ ግብረ ኃይል ሊያቋቁሙ መሆኑን የኢፌዴሪ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የሚቋቋመው የጋራ የፀጥታ ግብረ ኃይል (joint security task force) ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የገንዘብ ዝውውር፣ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ ሽብርተኝነት እና ሌሎች ድንበር ዘለል ወንጀሎችን ለመከላከል እና ለመግታት የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
በዛሬው እለት የጅቡቲ ብሔራዊ ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል አብዱላሂ አብዲ ፋራህ እና የኢፈዴሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ድንበር ተሻጋሪ እና የተደራጁ ወንጀሎችን በጋራ መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ የፖሊስ ተቋማት ለመጀመሪያ ጊዜ የጋራ ዘመቻ መሥራት የሚያስችላቸውን የጋራ የፀጥታ ግብረ ኃይል (joint security task force) በማቋቋም እና ተግባራዊ በማድረግ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የገንዘብ ዝውውር (የገንዘብ እጥበት)፣ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር፣ ሽብርተኝነት እና ሌሎች ድንበር ዘለል ወንጀሎችን ለመከላከል እና ለመግታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
በቀጣይ በጅቡቲ የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ለተግባራዊነቱ እንደሚሠራ የገለጹት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ቢሮዎችን በመክፈት የሁለቱም ሀገራት ፖሊስ ኦፊሰሮች በጋራ የሚሠሩበት እድል ይፈጠራል ብለዋል፡፡
የጅቡቲ ብሔራዊ ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል አብዱላሂ አብዲ ፋራህ በበኩላቸው፣ ለሰላም እና መረጋጋት ጠንቅ የሆኑ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል ያላቸውን የጋራ ራእያቸውን ማካፈል እንዲችሉ የኢፈዴሪ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ላቀረቡላቸው ጥሪ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት ትብብራቸውን የበለጠ በማጠናከርና በሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ የጋራ ግብረ ኃይል በማቋቋም እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የሁለቱም ሀገራት ፖሊስ መኮንኖች በአዲስ አበባ እንጦጦ አካባቢ የሚገኘውን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የአነፍናፊ ውሾች ካምፕ በመጎብኘት የልምድ ልውውጥ አድርገዋል፡፡
ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከል ረገድ የአነፍናፊ ውሾች ሥራ ለፖሊስ ተግባራት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል፣ በቀጣይ ክፍሉን ለማጠናከር ኮሚሽኑ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን መናገራቸውን ከኢፌዴሪ ፖሊስ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ተቋሙ በዚህ ዓመት በርካታ ቁጥር ያላቸው የአነፍናፊ ውሾች ግዥን ከተለያዩ ሀገራት ለመፈጸም በሂደት ላይ መሆኑንም ኮሚሽነር ጄነራሉ ገልጸዋል፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 117 ጥር 22 2013


