በአዲስ አበባ ከተማ በሕገ ወጥ መንገድ ለግለሰቦች ተላልፈው የተገኙ 21 ሺሕ ሕገ ወጥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ እንደሚወጣባቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
ከተማ አስተዳደሩ በአዲስ አበባ በተለያዩ ጊዜያት ተካሂደዋል ያላቸውን የመሬት ወረራዎች በጥናት ማረጋገጡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥር 18/2013 በሸራተን አዲስ ሆቴል በሰጡትጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል። ምክትል ከንቲባዋ መግለጫውን በሰጡበት ወቅት በሕገ ወጥ መንገድ ለግለሰቦች ተላልፈው የተገኙ 21 ሺሕ 697 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ እንዲወጣባቸው በምክር ቤት መወሰኑን አስታውቀዋል።
ምክትል ከንቲባዋ እንዳሉት ከሆነ እስካሁን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለተፈለገው አላማ በተገቢው መንገድ መዋል አለመቻላቸውን አመላክተዋል። አክለውም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዋና አላማ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የሕብረተሰብ ክፍል የቤት ተጠቃሚ ማድረግና መደጎም ቢሆንም እስካሁን የነበረው አሰራር ለባለሀብቶች እንጅ ለታሰበው የሕብረተሰብ ክፍል አለመዋሉን የጥናቱ ውጤት አመላካች ነው ብለዋል።
በመሆኑም በሕገ ወጥ መንገድ ተላልፈው የተገኙ 21 ሺሕ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከ1997 ጀምሮ ተስፋ ባለመቁረጥ ቁጠባቸውን እየቆጠቡ ለሚገኙ ጋራ መኖሪያ ቤት ቆጣቢዎች በእጣ እንደሚተላለፉ ውሳኔ መተላለፉን ተመላክቷል። እንደ ምክትል ከንቲበዋ ገለጻ በሕገ ወጥ ተላልፈው የተገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለቆጣቢዎች በእጣ እንዲተላለፉ በምክር ቤት ውሳኔ ከመተላለፉ በተጨማሪ በሕገ ወጦች ላይ የሕግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል። በዚሁ መሰረት ጉዳዩ ለጠቅላይ አቃቢ ሕግ እና ለከፍተኛ ፍርድ ቤት መረጃ መተላለፉንም ጨምረው ገልጸዋል።
ሕገ ወጥ መሆናቸውን በጥናት የተረጋገጡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ካርታ ይኑራቸው አንጅ ለግለሰቦቹ በምን ሁኔታ እንደተላለፉ ማስረጃ አለመገኘቱን ምክትል ከንቲባዋ ጠቁመዋል። የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ሕጋዊ አለመሆናቸውን በጥናቱ ላይ በሦስት መንገዶች ማረጋገጥ ተችሏል ተብሏል። አንደኛው ከቤቶች ኮርፖሬሽን መረጃ በመውሰድ ሲሆን ቤቶች ኮርፖሬሽን ስለ ቤቶቹ መረጃ የለውም። ኹለተኛው ከባንክ መረጃ በማውጣት ሲሆን በዚህም የተገኘ መረጃ የለም ተብሏል። ሦስተኛው ቤቶቹ በዕጣ የተላለፉበት ማስረጃ ሲሆን ይህም እንዳልተገኘ አዳነች ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የነዋሪውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ከ1997 ጀምሮ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት በተለያዩ ዙሮች በዕጣ ለተጠቃሚዎች ሲያስተላልፍ የቆየ ቢሆንም ለከተማ ነዋሪው ዋነኛ የቅሬታ ምንጭም ሆኖ ቆይቷል።
በመሆኑም በአጠቃላይ የቤት ማስተላለፍ ሂደት ችግሮችንና ተያያዥ ሕገ ወጥ ተግባራትን ለማጣራት የከተማ አስተዳደሩ በመወሰኑ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት በሳይንሳዊ አግባብ ዝርዝር ጥናት እንዲጠና አቅጣጫ ተቀምጦ ላለፉት ኹለት ወራት ጥናት ማድረጉን ከተማ አስተዳደሩ ገልጿል።
በጥናቱ ውጤት መሰረትም በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ የጋራ መኖርያ ቤቶች በጠቅላላው 21 ሺሕ 695 ሲሆኑ 16 ሺሕ 315 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ፣ አራት ሺሕ 530 ባዶ የሆኑ ( ያልተላለፉ)፣ 850 ዝግ የሆኑ ( በአንድ ወቅት ሰዎች የነበሩባቸው ሲሆን ረጅም ግዜ የተዘጉ) እና 424 በሕገ ወጥ መልኩ በግለሰቦች ተይዘው የሚገኙ ሲሆን የተላለፍበት ሁኔታ ሳይታወቅ ወደ ተጠቃሚው ግለሰቦች የተላለፉ ደግሞ 51 ሺሕ 64 ቤቶች ሆነው ተገኝተዋል ሲሉ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል።
በተጨማሪም በቤቶች ኮርፖሬሽን ተመዝግቦ የሚገኘው ባለዕጣዎች የስም ዝርዝር እና በመስክ በተገኘው የተጠቃሚዎች የስም ዝርዝር መሀከል ልዩነት ያላቸው ቤቶች 132 ሺሕ 678 እንደሆኑና የህም የሚያሳየው አጠቃላይ የተገነቡት ቤቶች ከ75 እጅ በላይ የሚሆነው ተጠቃሚ ኮንዶሚኒየም የተመዘገቡና የቆጠቡ አለመሆናቸውን የሚሳይ ሲሉ አዳነች ተናግረዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 117 ጥር 22 2013



